9ኛው ሀገር አቀፍ የጥራት ሽልማት የፊታችን ቅዳሜ ይካሄዳል - ኢዜአ አማርኛ
9ኛው ሀገር አቀፍ የጥራት ሽልማት የፊታችን ቅዳሜ ይካሄዳል
ጥቅምት 17 ቀን 2015 (ኢዜአ) 9ኛው ሀገር አቀፍ የጥራት ሽልማት የፊታችን ቅዳሜ በአዲስ አበባ እንደሚካሄድ የኢትዮጵያ ጥራት ሽልማት ድርጅት አስታወቀ።
የአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ ፕሬዝዳንትና የድርጅቱ የቦርድ ሰብሳቢ ፕሮፌሰር ጣሰው ወልደሀና ሽልማቱን አስመልክቶ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ አምራች ድርጅቶች፣ የህዝብ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት፣የትምህርትና የጤና ተቋማት፣በኮንስትራክሽን ዘርፍ የተሰማሩ እንዲሁም መንግስታዊ ያልሆኑ ሀገር በቀል ድርጅቶች ሽልማቱ የሚያካትታቸው ተቋማት እንደሆኑ ገልጸዋል።
አለምአቀፍ መለኪያዎች ወጥተው ለውድድሩ እንደ መወዳደሪያነት መቅረባቸውን ገልጸው በተቋማቱ የመስክ ምልከታ በማድረግ ዝርዝር ግምገማ መደረጉንም ጠቁመዋል።
የድርጅቱ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ቴዎድሮስ መብራት በበኩላቸው በጥራት ስራ አመራር የላቀ አፈጻጸም ያሳዩ ተቋማትና ድርጅቶችን መሸለምና እውቅና መስጠት እንዲሁም ጥራት የእያንዳንዱ ግለሰብና ተቋም መለኪያ እንዲሆን የጥራትን ጽንሰ ሀሳብ በህብረተሰቡ ዘንድ ማስረጽ የድርጅቱ አላማ ነው ብለዋል።
በተለያዩ መንገዶች ጥሪ ከተደረገላቸው ድርጅቶች እና ተቋማት ውስጥ 45 የሚሆኑ ድርጅቶች የተመዘገቡ ሲሆን 40 የሚሆኑት ድርጅቶች እስከ ውድድሩ መጨረሻ መድረሳቸውን ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ጥራት ሽልማት ድርጅት በአዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ እና በዋልታ ሚዲያና ኮሙዩኒኬሽን ኮርፖሬት አማካኝነት በ2000 ዓ.ም ነው የተቋቋመው።