ባለፉት ስድስት ወራት ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ድጋፍ የሚሆን ከ21 ሚሊዮን ብር በላይ ተሰብስቧል-ዞኑ - ኢዜአ አማርኛ
ባለፉት ስድስት ወራት ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ድጋፍ የሚሆን ከ21 ሚሊዮን ብር በላይ ተሰብስቧል-ዞኑ
አምቦ ጥቅምት 17 ቀን 2015 በምዕራብ ሸዋ ዞን ባለፉት ስድስት ወራት ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ድጋፍ የሚሆን ከ21 ሚሊዮን ብር በላይ መሰብሰቡን የዞኑ የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጽህፈት ቤት አስታወቀ።
የጽህፈት ቤቱ ተወካይ አቶ ወርቅነህ ሁንዴሳ ለኢዜአ እንዳስታወቁት፤ የዞኑ ነዋሪዎች ለግድቡ ግንባታ በቦንድ ግዥና በስጦታ አስተዋፅኦ ሲያደርጉ ቆይተዋል።
ባለፉት ስድስት ወራት በዞኑ ሁሉም ወረዳዎች በተደረገ እንቅስቃሴ ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች በቦንድ ግዢና ስጦታ 15 ሚሊዮን ብር ለመሰብሰብ ታቅዶ 21 ነጥብ 2 ሚሊዮን ብር በላይ መሰብሰቡን ነው የተናገሩት፡፡
በየደረጃው ያለው አመራር የግድቡ ግንባታ መጠናቀቅ ያለውን ሀገራዊ ፋይዳ በመረዳት ህዝቡን በማስተባበር ከፍተኛ ስራ ሲሰሩ መቆየቱንም ተናግረዋል።
ከዚህም ከተሰበሰበው ገቢ ከ18 ሚሊዮን ብር በላይ ከቦንድ ጊዢ የተገኘ ሲሆን 3 ሚሊየን ብር በስጦታ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
የታላቁ ህዳሴ ግድብ ዋንጫ ሰሞኑን ወደ ምዕራብ ሸዋ ዞን የሚገባ ሲሆን ለአቀባበሉ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑንም ተመልክቷል።
የግድቡ መሰረት ከተጣለበት ቀን ጀምሮ በዞኑ ከመንግስት ሰራተኞች፣ ባለሀብቶች፣ አርሶ አደሮችና ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎች በቦንድ ሽያጭና በስጦታ 95 ሚሊየን ብር በላይ መሰብሰቡን አስታውሰዋል።