አንዳንድ ምዕራባውያን አገራት እና ተቋማት በኢትዮጵያ ላይ የሚሳድሩትን ጫና የሚቃወም ሰልፍ በስፔን ሊካሄድ ነው - ኢዜአ አማርኛ
አንዳንድ ምዕራባውያን አገራት እና ተቋማት በኢትዮጵያ ላይ የሚሳድሩትን ጫና የሚቃወም ሰልፍ በስፔን ሊካሄድ ነው
ጥቅምት 17 ቀን 2015 (ኢዜአ) አንዳንድ ምዕራባውያን አገራት በኢትዮጵያ ላይ የሚያደርጉትን ጣልቃ ገብነት እና ጫና የሚቃወም ሰልፍ በስፔን ማድሪድ ከተማ የፊታችን እሁድ ይካሄዳል።
በማድሪድ ከተማ በሚገኘው የአውሮፓ ሕብረት ቢሮ በሚካሄደው ሰልፍ ኢትዮጵያውያን፣ ትውልደ-ኢትዮጵያውያን፣ የስፔን ተወላጆች እና የኢትዮጵያ ወዳጆች እንደሚሳተፉበት ተገልጿል።
በሰልፉ ላይ የአውሮፓ ሕብረት በኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ ላይ የያዘውን የተዛባና ሚዛናዊነት የጎደለው አቋም እንዲያስተካክል ጥሪ የሚያቀርቡ መልዕክቶች እንደሚተላለፉ የ“ዲፌንድ ኢትዮጵያ ታስክ ፎርስ ኢሮፕ” የስፔን ቻፕተር አስተባባሪ አቶ ታረቀኝ አስናቀ ለኢዜአ ገልጸዋል።
የሕብረቱ አንዳንድ ባለስልጣናት ከተቋሙ እሴቶች ባፈነገጠ መልኩ ኢትዮጵያን አስመልክቶ ከሚሰጧቸው አሉታዊ አስተያየቶች ሊቆጠቡ እንደሚገባ የሚያሳስቡ መፈክሮች እንደሚሰሙም ተናግረዋል።
የአውሮፓ ሕብረትና ዓለም አቀፍ ተቋማት በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም እንዲመጣ ከኢትዮጵያ ሕዝብና መንግስት ጎን መቆም ይኖርባቸዋል ብለዋል።
የሰልፉ አስተባባሪዎች በስፔን የአውሮፓ ሕብረት ተወካዮች ጣልቃ ገብተነትና ጫናውን የሚቃወም ደብዳቤ እንደሚያስገቡም አቶ ታረቀኝ ገልጸዋል።
በስፔን የሚኖሩ የኢትዮጵያ ማህበረሰብ አባላት የአገራቸውን ብሔራዊ ጥቅም የሚያስጠብቁ የፐብሊክ ዲፕሎማሲና የመልሶ ማቋቋም ስራዎች እያከናወኑ እንደሚገኝ አመልክተዋል።