ቀጥታ፡

በሕገ-ወጥ መንገድ ከ5 ቢሊየን ብር በላይ ሲያንቀሳቅስ የነበረ ግለሰብ በቁጥጥር ስር መዋሉ ተገለፀ

ጥቅምት 16 ቀን 2015 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ በህገ-ወጥ መንገድ ከ5 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር በላይ ሲያንቀሳቅስ የነበረ ግለሰብ ከ25 ግብረ-አበሮቹ ጋር በቁጥጥር ስር አውሎ ምርመራ እያጣራባቸው መሆኑን ገለፀ፡፡

በወንጀሉ የተጠረጠረው ሳሙኤል እጓለ አለሙ በቅፅል ስሙ ሳሚ ዶላር የሚባል ሲሆን ነዋሪነቱን በአዲስ አበባ ከተማ በማድረግ ወደ አሜሪካ በተደጋጋሚ ይመላለስ እንደነበር ተገልጿል።

ግለሰቡ የኤሌክትሪክ መሳሪያዎች፣ የቤት እና የቢሮ እቃዎች እንዲሁም ተዛማጅ መገልገያዎች የችርቻሮ ንግድ ፍቃድን ሽፋን በማድረግ ሕገ-ወጥ የውጭ ምንዛሬና በሕገ-ወጥ የገንዘብ ዝውውር ወንጀል ተጠርጥሮ በራሱና ዮዲት እጓለ አለሙ ከተባለች እህቱ ጋር በመሆን በስማቸው በተለያዩ ባንኮች በከፈቷቸው 25 የባንክ አካውንቶች በአንድ ዓመት ውስጥ ከ247 ሚሊየን ብር በላይ ማንቀሳቀሳቸውን ፖሊስ ደርሶባቸው ምርመራ እየተጣራባቸው መሆኑ ታውቋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም ግለሰቡ ከ25 አምስቱ የወንጀል ግብረ-አበሮቹ ጋር በመሆን በህገ-ወጥ መንገድ ከ5 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር በላይ ሲያንቀሳቅሱ እንደነበር በቅድመ ምርመራ ተደርሶባቸዋል፡፡

ተጠርጣሪዎቹ በሕገ-ወጥ የውጭ ሀገር የገንዘብ ዝውውር፣ በግብር ስወራ ወንጀል እና ከህወሃት የሽብር ቡድን ጋር የግንኙነት መረብ በመፍጠር ከፍተኛ ገንዘብ ሲያዘዋውሩ እንደነበር ተጠርጥረው ምርመራ እየተካሄደባቸው ይገኛል፡፡

ተጠርጣሪዎቹ በአጠቃላይ በ1 ዓመት ውስጥ 5 ቢሊዮን 2 መቶ 45 ሚሊየን ብር በላይ በሕገ-ወጥ መንገድ ሲያንቀሳቅሱ እንደነበር ፖሊስ ባደረገው ምርመራ ደርሶባቸዋል።

በመጨረሻም ተጠርጣሪዎቹ በቁጥጥር ሥር እንዲውሉ ኅብረተሰቡ ላደረገው ቀና ትብብር ተቋሙ ምስጋና አቅርቧል።

ኅብረተሰቡ ተመሳሳይ የወንጀል ድርጊት ሲያጋጥም በአፋጣኝ በስልክ ቁጥሮች 0115 30 91 39፣ 0111 11 94 75፣ 0111 71 10 12 እንዲሁም 816 ነፃ የስልክ መስመር በመጠቀም ጥቆማ በመስጠት የተለመደ ድጋፍና ትብብር እንዲያደርግ ጥሪ አስተላልፏል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም