ቀጥታ፡

በወረዳው ካለው የመንገድ መሰረተ-ልማት ችግር አኳያ የዲዛይን ለውጥ ማድረጉ አማራጭ የሌለው ውሳኔ ነው- ርዕሰ-መስተዳድር ኡሞድ ኡጁሉ

ጋምቤላ ጥቅምት 16/2015 (ኢዜአ) በወረዳው ካለው የመንገድ መሰረተ-ልማት ችግር አኳያ የዲዛይን ለውጥ ማድረጉ አማራጭ የሌለው ውሳኔ መሆኑን የጋምቤላ ክልል ርዕሰ-መስተዳድር አቶ ኡሞድ ኡጁሉ ተናገሩ።

የጋምቤላ ሕዝቦች ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት መስተዳድር ምክር ቤት ሥራ አስፈጻሚ ዛሬ ባካሄደው ስብሰባ የአንድ የመንገድ ፕሮጀክት የዲዛይን ማሻሻያን ተቀብሎ አጽድቋል።

ሥራ አስፈጻሚው የዲዛይን ማሻሻያ እንዲደረግበት ውሳኔ ያሳለፈው ከጆር - አንጌላ - አኮቦ ባለው የ81 ኪሎ ሜትር የመንገድ ፕሮጀክትን ነው።

በተለይም የአኮቦና የጆር ወረዳዎች ባለፉት ዓመታት የመንገድ መሰረተ-ልማት ተጠቃሚ ሳይሆኑ መቆየታቸውን ርዕሰ-መስተዳድሩ አስታውሰዋል።

የመንገድ ፕሮጀክቱ ቀደም ሲል ዲዛይኑ በአስፓልት ደረጃ ተዘጋጅቶ የነበረ ቢሆንም የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር ባቀረበው ምክር ሃሳብ ዲዛይኑ ወደ ጠጠር መንገድ እንዲቀየር ስራ አስፈጻሚው ውስኗል።

የመንገድ ፕሮጀክቱ የዲዛይን ለውጥ ማድረግ ያስፈለገበት ምክንያት የአካባቢው መልክዓ ምድር አስቸጋሪ በመሆኑና የግንባታው ሂደት ከ13 ዓመታት በላይ የሚፈጅ መሆኑን በኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር ባለሙያዎች ማብራሪያ ተሰጥቷል።

አዲስ በተቀየረው ዲዛይን መሰረት የመንገድ ፕሮጀክቱ የግንባታ ሂደት በአራት ዓመት ጊዜ ውስጥ  ሊጠናቀቅ እንደሚችልም በማብራሪያቸው ገልጸዋለ።

በአስተዳደሩ የዲዛይን ዳይሬክቶሬት ዳሬክተር ኢንጅነር ፍሬው በቀለ በመድረኩ እንዳሉት፣ መንገዱ የሚገነባበት አካባቢ ዝቅተኛ በመሆኑና ለረጅም ጊዜ ውሃ ስለሚተኛበት በዓመት ለሥራ ምቹ የሆነው ጊዜ አራት ወር ብቻ ነው።

በተጨማሪም ለመንገዱ የሚሆን የአፈር ሙሌት የሚመጣበት አካባቢ ከ100 ኪሎ ሜትር በሚበልጥ ርቀት ላይ የሚገኝ መሆኑና በሌሎች ምክንያቶች ተደጋጋሚ ጨረታዎች ቢወጡም ሥራ ተቋራጭ አለመገኘቱን ተናግረዋል።

በአሥር ዓመቱ የመንገድ ልማት ዕቅድ ወረዳዎቹን ተጠቃሚ ለማድረግ መሰራት እንዳለበት ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር በጋምቤላ ክልል ከ10 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር በሚበልጥ ወጪ የሰባት አስፓልት መንገዶች ግንባታ እያካሄደ ነው።

አስተዳደሩ ለመንገድ ፕሮጀክቶቹ ግንባታ ስኬታማነት የጋምቤላ አካባቢ የኮንስትራክሽን ማኔጅመንት ጽህፈት ቤት መክፈቱም ተመላክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም