ቀጥታ፡

የኢትዮጵያን ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነት በማክበር የውስጥ ችግሯን በራሷ አቅም እንድትፈታ ማገዝ ይገባል--አምባሳደር ሽሪ ሮበርት ሼትኪንቶንግ

ጥቅምት 16 ቀን 2015 (ኢዜአ) የኢትዮጵያን ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነት በማክበር የውስጥ ችግሯን በራሷ አቅም እንድትፈታ ማገዝ እንደሚገባ በኢትዮጵያ የህንድ አምባሳደር ሽሪ ሮበርት ሼትኪንቶንግ ገለጹ፡፡

አምባሳደሩ ለኢዜአ እንዳሉት፤ ኢትዮጵያና ህንድ ከ200 ዓመት በላይ የዘለቀ ጠንካራ ትብብርና ወዳጅነት ያላቸው ሀገሮች ናቸው፡፡

በሁለቱ ሀገሮች መካከል ያለው የባህል፣ የትምህርት፣ የንግድና ኢንቨስትመንት፣ የማምረቻ ኢንዱስትሪ ልማት ግንኙነት በመርህ ላይ የተመሰረተ መሆኑን ጠቅሰው፤ ሀገራቱ ከሁለትዮሽ ግንኙነት ባሻገር በዓለም አቀፍ መድረኮችም ተመሳሳይ አቋም እንደሚያራምዱ ተናግረዋል።

ህንድ በአሁኑ ወቅት ተለዋጭ አባል በሆነችበት የፀጥታው ምክር ቤት ሪፎርም ማድረግ የሚገባው ጉዳዮች ላይም ሁለቱ ሀገሮች ተመሳሳይ አካሄድ እንደሚከተሉና መደጋገፍ እንደሚያሳዩም ገልጸዋል፡፡

ለአብነትም ኢትዮጵያ በሰሜን የሀገሪቱ ክፍል የተከሰተውን ግጭት በሰላማዊ አማራጭ ለመፍታት እያደረገች ያለውን ጥረት ሀገራቸው እንደምትደግፍና ተመሳሳይ አቋም እንዳላት ጠቅሰዋል።

ህንድ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነትን በማክበር በሁለቱ ሀገሮች መካከል በመርህ ላይ የተመሰረተ ጠንካራ ግንኙነት መፍጠሯንም ነው አምባሳደር ሽሪ ሮበርት ሼትኪንቶንግ የተናገሩት፡፡

በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ላይ የሚነሳውን ልዩነት ሶስቱ ሀገራት ለአፍሪካውያን ችግር አፍሪካዊ መፍትሔ በሚለው መርህ በውይይት መፍታት እንደሚችሉም ጠቁመዋል።

ኢትዮጵያ በውስጧ የተከሰቱ ችግሮችን በራሷ የመፍታት አቅም እንዳላት እናምናለን ያሉት አምባሳደሩ፤ ለዚህ ስኬት የኢትዮጵያን የግዛት አንድነትና ሉዓላዊነት ማክበር ይገባልም ብለዋል፡፡

በህንድ የኢትዮጵያ አምባሳደር ትዝታ ሙሉጌታ በበኩላቸው ኢትዮጵያና ህንድ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ በትብብር እየሰሩ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በሰብዓዊ ድጋፍ፣ በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ፣ በሰሜን ኢትዮጵያ ግጭት ዙሪያ ህንድ ከኢትዮጵያ ጎን በመቆም አጋርነቷን አሳይታለች ብለዋል፡፡

በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤትና በሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን በኢትዮጵያ ጉዳዮች ላይ በተደረጉ ስብሰባዎች ወዳጅነትን የሚያንጸባርቅ አቋም ማሳየቷንም ጠቅሰዋል።

በኢትዮጵያ ከ650 በላይ የህንድ ኩባንያዎች በተለያዩ የኢንቨስትመንት ዘርፎች የተሰማሩ ሲሆን የኢንቨስትመንቱ መጠንም ከ5 ቢሊየን ዶላር በላይ መድረሱን ተመላክቷል።

የህንድ ኩባንያዎች ከ75 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ኢትዮጵያውያን የስራ እድል በመፍጠር በሀገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ የጎላ ተሳትፎ እያደረጉ መሆኑም ተገልጿል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም