ለሳይንስና ቴክኖሎጂ የተሰጠው ትኩረት ለሁለንተናዊ እድገት መሰረት የሚጥል ነው-የስፔስ ሳይንስና ጂኦስፓሻል ኢንስቲትዩት - ኢዜአ አማርኛ
ለሳይንስና ቴክኖሎጂ የተሰጠው ትኩረት ለሁለንተናዊ እድገት መሰረት የሚጥል ነው-የስፔስ ሳይንስና ጂኦስፓሻል ኢንስቲትዩት
ጥቅምት 16/2015(ኢዜአ) ኢትዮጵያ ለሳይንስና ቴክኖሎጂ የሰጠችው ትኩረት የውጭ ተጋላጭነትን በማስቀረት ለሁለንተናዊ እድገት መሰረት የሚጥል መሆኑን የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስና ጂኦስፓሻል ኢንስቲትዩት ገለፀ።
ዓለም በእንፋሎት፣ በኤሌክትሪክ፣ በአይሲቲ ዘመን የሚሰኙ የኢንዱስትሪ አብዮቶችን አልፋ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስና ዘመነ ኢንተርኔትን ባካተተው 'መጻዒ ጊዜ' በተባለ የኢንዱስትሪ አብዮት ላይ ደርሳለች።
በሳይንስና በቴክኖሎጂ የተራቀቁ አገራትም ከመሬት አልፈው በጨረቃ ላይ እሸቅድድም ገብተዋል፤ እየተሻሻለ የመጣውም የሰው ልጆች የዕለት ከዕለት ኑሮ ቴክኖሎጂ መራሽ ሆኗል።
በኢትዮጵያም ለብዙ ዓመታት ትኩረት ተነፍጎት የቆየውን ዘርፍ ከ2009 ዓ.ም ወዲህ ሰፋፊ እንቅስቃሴዎችን በማድረግ ተጨባጭ ውጤቶችን እያመጣች መሆኑን የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስና ጂኦስፓሻል ኢንስቲትዩት አስታውቋል።
የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር አብዲሳ ይልማ ለኢዜአ እንደገለጹት በሕዋ ሳይንስ መስክ በተደረጉ ክንውኖች ለግብርና፣ በቱሪዝም፣ በጤና እና በሌሎች መስኮች ለውጤት የሚጠቅሙ ግብዓቶች እየተገኙበት ይገኛል።
ወጣቱ ለአገር ሁለንተናዊ እድገት አስተዋጽኦ እንዲያበረክት የሳይንስና ቴክኖሎጂ ክህሎት እንዲኖረው መስራት ይገባል ብለዋል።
በቅርቡ የተመረቁ የሳይንስ ሙዚየም እና በቡራዩ ከተማ የተገነባው የተሰጥኦ ማበልጸጊያ ትምህርት ቤት የነገን ትውልድ ለመቅረጽ በተለይም ለባለተሰጥኦ ወጣቶች የሕልም ስኬት መሆኑን አስረድተዋል።
የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስና ጂኦስፓሻል ኢንስቲትዩት ከሁለት ዓመታት በፊት የኢትዮጵያ ታዳጊዎች የስፔስ ሳይንስ ማዕከል አቋቁሞ ልዩ ተሰጥኦ ያላቸውን ታዳጊዎች እያሰለጠነ መሆኑንም ተናግረዋል።
ማዕከሉ ከአዲስ አበባ በተጨማሪ ከአምቦና ከደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲዎች ጋር በመቀናጀት ተደራሸነቱን እያሰፋ፣ የባለተሰጥኦ ታዳጊዎችን ህልሞችም ወደ ውጤት እንዲለውጡ እገዛ እያደረገ መሆኑን ጠቅሰዋል።
ለአፍሪካዊያን የነጻነት ተምሳሌት ተደርጋ የምትወሰደው ኢትዮጵያ በተለይም በኢኮኖሚ ራሷን አለመቻሏና በቴክኖሎጂ ወደ ፊት ሳትራመድ መቆየቷ በምዕራባዊያን ዘንድ መልከ ብዙ ተጽዕኖዎች እንድትጋለጥ ያደረጋት መሆኑን አብራርተዋል።
በመሆኑም በኢኮኖሚው መስክ ሉዓላዊነቷን ለማስከበር በሳይንስና ቴክኖሎጂ ብዙ እርቀት መራመድ ስላለባት አሁናዊ ጅምሮቿም የውጭ ተጋላጭነቷን ለመቀነስ መሰረት ሆኗል ብለዋል።
የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ የልማት እንቅስቃሴዎች ውጤታማነት ለማስቀጠል በሳይንስና ቴክኖሎጂ ግኝቶች በመደገፍ መስራት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።