ከአላማጣ ቆቦ እና ከአላማጣ ላልይበላ ያለው የኤሌክትሪክ ማስተላለፊያ መስመር ጥገና በአንድ ሳምንት ለማጠናቀቅ እየተሰራ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ከአላማጣ ቆቦ እና ከአላማጣ ላልይበላ ያለው የኤሌክትሪክ ማስተላለፊያ መስመር ጥገና በአንድ ሳምንት ለማጠናቀቅ እየተሰራ ነው
ጥቅምት 16 ቀን 2015 (ኢዜአ) ከአላማጣ እስከ ቆቦ እና ከአላማጣ እስከ ላልይበላ ያለው የኤሌክትርክ ማስተላለፊያ መስመር ጥገና ስራን በአንድ ሳምንት ውስጥ ለማጠናቀቅ እየተሰራ መሆኑን በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የወልዲያ ዲስትሪክት አስታወቀ።
አሸባሪው የህወሃት ቡድን በከፈተው ጦርነት የተጎዱ የኤሌክትሪክ መሰረተ-ልማቶችን የመጠገን ሥራ ተጠናክሮ መቀጠሉንም የዲስትሪክቱ ዳይሬክተር አቶ ሽመልስ ወልደሰማያት ገልጸዋል።
በአካባቢው በሚገኙ የኤሌክትሪክ መሰረተ-ልማቶች ላይ ከፍተኛ ጉዳት እንደደረሰባቸው ጠቁመዋል፡፡
በዚህም በሰሜን ወሎ አካባቢ 10 የኤሌክትሪክ ኮንክሪት ምሰሶዎችና ከ46 ትራንስፎርመሮች በላይ ከፍተኛ ጉዳት እንደደረሰባቸውና በአካባቢው ለመስኖ ፕሮጀክት የተተከሉ የእንጨት ምሰሶችም ከጥቅም ውጭ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
አቶ ሽመልስ ከአላማጣ እስከ ቆቦ እየተከናወነ የሚገኘው የመካከለኛ መስመር የጥገና ስራ 50 በመቶ መጠናቀቁንና የ66 ኪሎ ቮልት የሀይል ማስተላለፊያ ወይም ትራንስሚሽን መስመር ጥገና ስራ መጀመሩን ነው የገለጹት፡፡
የጥገና ሥራው በሁለት ምድብ ተከፍሎ እየተከናወነ መሆኑን የገለፁት አቶ ሽመልስ፤ በአንድ ሳምንት ጊዜ ውስጥ ጥገናውን ለማጠናቀቅ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የተቋረጠውን የኤሌክትሪክ አገልግሎት በአጭር ጊዜ ለመመለስ ርብርብ እየተደረገ ነው ያሉት ዳይሬክተሩ፤ በኤሌክትሪክ ማስተላለፊያ መስመሮች ጋር የተገናኙ የዛፍ ቅርንጫፎችን የሚመለከታቸው የአስተዳድር አካላት ህብረተሰቡን በማስተባበር የምንጣሮ ስራ እንዲያከናውኑ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
ከአሸባሪው ህወሓት ነጻ በወጡ አካባቢዎች የኤሌክትሪክ አገልግሎት ለማስጀመር በጥናት ላይ የተመሰረተ ስራ እየተሰራ መሆኑን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል መግለጹን ኢዜአ መዘገቡ ይታወሳል።