ቀጥታ፡

በጋምቤላ ክልል ከ10 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ የሰባት መንገዶች ግንባታ እየተካሄደ ነው-አስተዳደሩ

ጥቅምት 16 ቀን 2015 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር በጋምቤላ ክልል ከ10 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ የሰባት አስፓልት መንገዶች ግንባታ እያካሄደ መሆኑን አስታወቀ።

አስተዳደሩ ለመንገዶቹ ግንባታ ስኬታማነት የጋምቤላ አካባቢ የኮንስትራክሽን ማኔጅመንት ጽህፈት ቤት መክፈቱን አስታውቋል።

የጽህፈት ቤቱ ስራ አስኪያጅ ኢንጂነር ሰለሞን ታደሰ ለኢዜአ እንደገለጹት አስተዳደሩ በክልሉ ከ500 ኪሎ ሜትር በላይ ርዝመት ያላቸው ሰባት የአስፓልት መንገዶች እየገነባ ነው።

በመገንባት ላይ ከሚገኙት መንገዶች መካከል ከጋምቤላ አቦቦ ፑኚዶ፣ ከፑኝዶ ጊሎ ወንዝ ፣ ከፑኝዶ ጆር ፣ከላሬ ኝንኛንግ እንደሚገኙበት ጠቅሰዋል።

ከመንገዶቹ መካከልም ከአበቦ ወደ ማጃንግ ዞን የሚወስደው የ76 ኪሎ ሜትር የአስፓልት ስራ በመጠናቀቅ ላይ መሆኑን ጠቁመው ቀሪዎቹ በተለያዩ የአፈፃፀም ደረጃ ላይ እንደሚኙ ተናግረዋል።

መንገዶቹ ዞኖችን ከክልሉ ማዕከልና ዞኖችን ከወረዳዎች ጋር የሚያገናኙ መሆናቸውን ጠቁመው ግንባታውን በቅርበት በመከታተል በጥራት፣ በተያዘላቸው ጊዜና በጀት ለማጠናቀቅ በቅርበት እየተሰራ ነው ብለዋል።

ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቱ በቀጣይም በክልሉ በአስር ዓመቱ የመንገድ መሰረተ ልማት ስትራቴጂክ እቅድ ስኬታማነት የጎላ ፋይዳ እንደሚኖረው ስራ አስኪያጁ ጠቁመዋል።

የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር የመሰረተ ልማት አማካሪ አቶ ኡሞድ ኡሞድ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቱ መከፈቱን አስመልክተው እንዳሉት ካሁን በፊት በክልሉ በመንገድ ዙሪያ የሚያጋጥሙ ችግሮችን በቅርበት መፍትሄ ለመስጠት ያስችላል።

በጽህፈት ቤቱ መከፈት የክልሉ መንግስት ደስተኛ መሆኑን ነው የጠቀሱት።

አስተዳደሩ ለጀመራቸው ስራዎች መሳካት ሁለንተናዊ ድጋፍ ለመስጠት ዝግጁ መሆኑንም ገልጸዋል።

“የአስተዳደሩ ጽህፍት ቤት መክፈቱ የፕሮጀክቶችን አፈጻጸም ሄደት ያፋጥናል” ያሉት ደግሞ የፑኝዶ ጊሎ ወንዝ የመንገድ ፕሮጀክት አማካሪ ኢንጂነር ግዛቸው ጌቴ ናቸው።

የፑኝዶ ጆር አኮቦ የመንገድ ተቋራጭ ተጠሪ መሃንዲስ ኢንጅነር ሙሐመድ ሳዲክ “የጽህፈት ቤቱ መከፈት ቀደም ሲል የፕሮጀክቱን የአፈፃፀም ሂደት ለመገምገም ሆነ ክፍያ ለመጠየቅ የሚፈጀውን ጉልበትና ጊዜ የሚያስቀር ነው” ብለዋል።

አስተዳደሩ ባለፈው ሳምንት ነበር የጋምቤላ አካባቢ የኮንስትራክሽን ማኔጅመንት ጽህፈት ቤቱን በይፋ ከፍቶ ስራ የጀመረው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም