የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶችና ተላላኪዎች የብጥብጥ ዒላማ የነበረው የመተከል ዞን ዛሬ ላይ የሰላምና የልማት ተስፋ የሚታይበት ሆኗል-ርዕሰ መስተዳድር አሻድሊ ሀሰን - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶችና ተላላኪዎች የብጥብጥ ዒላማ የነበረው የመተከል ዞን ዛሬ ላይ የሰላምና የልማት ተስፋ የሚታይበት ሆኗል-ርዕሰ መስተዳድር አሻድሊ ሀሰን

ጥቅምት 16/2015 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶችና ተላላኪዎች ዋነኛ የብጥብጥ ዒላማ የነበረው የመተከል ዞን ዛሬ ላይ የሰላምና የልማት ተስፋ የሚታይበት አካባቢ መሆኑን የቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አሻድሊ ሀሰን ገለፁ።
ርዕሰ መስተዳድሩ ይህን ያሉት በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከል ዞን ግልገል በለስ ከተማ ባዘጋጀው "ስለ ኢትዮጵያ" የፓናል ውይይት ላይ ነው።
የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ እንዲስተጓጎል የሚሹ የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች በአገር ውስጥ ተላላኪዎችን በማሰማራት የጸጥታ ችግር ሲፈጥሩ ቆይተዋል ብለዋል፡፡
በተለይ በመተከል ዞን በሰው ህይወትና ንብረት ላይ ጉዳት ማድረሳቸውን አስታውሰዋል፡፡
ይሁን እንጂ ኢትዮጵያ የገጠሟትን ፈተናዎች ተጋፍጣ በአንድ በኩል ልማቷን በማስቀጠል በሌላ በኩል ደግሞ ፈተናዎችን ወደ ዕድል በመቀየር ዘርፈ-ብዙ ስኬት እያስመዘገበች ነው ብለዋል።
ከዚህ ቀደም የፀጥታ ችግር የነበረበት የመተከል ዞን አሁን ወደ ሰላምና መረጋጋት መምጣቱን ጠቅሰው፤ አሁን ላይ በአካባቢው ሰላም መስፈኑንና የልማት ስራዎች እየተከናወኑ ይገኛል ሲሉ ተናግረዋል።
ይህም ኢትዮጵያ ፈተናዎቿን በአሸናፊነት እንደምትሻገር አንዱ ማሳያ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ዋና ሥራ አስፈጻሚ ጌትነት ታደሰ በበኩላቸው፤ የመተከል ዞን አሁን ላይ የተረጋጋና ሕዳሴ ግድብን ጨምሮ የኢትዮጵያ የልማት ብሥራት ሥፍራ ሆኗል ብለዋል፡፡
የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ሥራ አስኪያጅ ኢንጂነር ክፍሌ ሆሮ፤ ኢትዮጵያ ችግሮችን ተቋቁማ የመሻገር አቅም እንዳላት አንስተው ለአብነትም የሕዳሴ ግድብ ፕሮጀክትን ለማሰናከል ጠላቶች በየጊዜው ያደረጉት ሙከራ ያለመሳካትና ግድቡ አሁን ያለበት ደረጃ መድረስ ይህን የሚያመላክት ነው ብለዋል።
ግድቡ በኮንክሪት ብቻ ሳይሆን በኢትዮጵያዊያን ደም ጭምር የተገነባ መሆኑን ጠቅሰው፤ ግድቡ ሙሉ ለሙሉ እስኪጠናቀቅ ኢትዮጵያዊያን በትብብር ድጋፍ ማድረግ እንዳለባቸው ተናግረዋል፡፡
ኢትዮጵያን ለማፍረስ ለዘመናት ብዙ ተሞክሯል፤ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊያን ግን የገጠሟቸውን ፈተናዎች በአሸናፊነት አልፈዋል ያሉት ደግሞ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፓለቲካ ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህር እንዲሁም የአባይ ውሃ ተመራማሪ ዶክተር ያዕቆብ አርሳኖ ናቸው፡፡
አሁን ላይ ያለው ብቸኛ መንገድ ኢትዮጵያን ማልማትና ማበልፀግ መሆኑንም ነው ያብራሩት፡፡