የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶችና ተላላኪዎች የብጥብጥ ዒላማ የነበረው የመተከል ዞን አሁን የሰላምና የልማት ተስፋ የሚታይበት ሆኗል--የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ-መስተዳድር - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶችና ተላላኪዎች የብጥብጥ ዒላማ የነበረው የመተከል ዞን አሁን የሰላምና የልማት ተስፋ የሚታይበት ሆኗል--የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ-መስተዳድር
ጥቅምት 16/2015 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶችና ተላላኪዎች ዋነኛ የብጥብጥ ዒላማ የነበረው የመተከል ዞን ዛሬ ላይ የሰላምና የልማት ተስፋ የሚታይበት አካባቢ መሆኑን የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ-መስተዳድር አሻድሊ ሀሰን ገለፁ።
ርዕሰ-መስተዳድሩ ይህን ያሉት በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከል ዞን ግልገል በለስ ከተማ ባዘጋጀው "ስለ ኢትዮጵያ" የፓናል ውይይት ላይ ነው።
የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ እንዲስተጓጎል የሚሹ የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች የሀገር ውስጥ ተላላኪዎችን በማሰማራት የጸጥታ ችግር ሲፈጥሩ ቆይተዋል ብለዋል፡፡
በተለይ በመተከል ዞን በሰው ህይወትና ንብረት ላይ ጉዳት ማድረሳቸውን አስታውሰዋል፡፡
ይሁን እንጂ ኢትዮጵያ የገጠሟትን ፈተናዎች ተጋፍጣ በአንድ በኩል ልማቷን በማስቀጠል በሌላ በኩል ደግሞ ፈተናዎችን ወደ ዕድል በመቀየር ዘርፈ-ብዙ ስኬት እያስመዘገበች ነው ብለዋል።
ከዚህ ቀደም የፀጥታ ችግር የነበረበት የመተከል ዞን ወደ ሰላምና መረጋጋት መምጣቱን ጠቅሰው፤ አሁን ላይ በአካባቢው ሰላም መስፈኑንና የልማት ስራዎች እየተከናወኑ እንደሚገኙ ተናግረዋል።
ይህም ኢትዮጵያ ፈተናዎቿን በአሸናፊነት እንደምትሻገር አንዱ ማሳያ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ሥራ አስኪያጅ ኢንጂነር ክፍሌ ሆሮ፤ ኢትዮጵያ ችግሮችን ተቋቁማ የመሻገር አቅም እንዳላት አንስተዋል።
የሕዳሴ ግድብ ፕሮጀክትን ለማሰናከል በየጊዜው የተደረጉ ሙከራዎች ያለመሳካትና ግድቡ አሁን ላለበት ደረጃ መድረስ ይህንኑ የሚያመላክት ነው ብለዋል።
ግድቡ በኮንክሪት ብቻ ሳይሆን በኢትዮጵያውያን ደም ጭምር የተገነባ መሆኑን ጠቅሰው፤ ግድቡ ሙሉ ለሙሉ እስኪጠናቀቅ ኢትዮጵያውያን ድጋፋቸውን ማጠናከር እንዳለባቸው ተናግረዋል፡፡
ኢትዮጵያን ለማፍረስ ለዘመናት ብዙ ተሞክሯል፤ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን ግን የገጠሟቸውን ፈተናዎች በአሸናፊነት አልፈዋል ያሉት ደግሞ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፓለቲካ ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህር እንዲሁም የአባይ ውሃ ተመራማሪ ዶክተር ያዕቆብ አርሳኖ ናቸው፡፡
አሁን ላይ ያለው ብቸኛ መንገድ ኢትዮጵያን ማልማትና ማበልፀግ መሆኑንም ነው ያብራሩት፡፡