ቀጥታ፡

መንግሥት በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል የተቀሰቀሰውን ግጭት በዘላቂነት ለመፍታት ቅድሚያ ሰጥቶ እየሰራ ነው-አምባሳደር ተሾመ ቶጋ

ጥቅምት 16/2015(ኢዜአ) መንግሥት በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል የተቀሰቀሰውን ግጭት በዘላቂነት ለመፍታት ለሰላም ቅድሚያ ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን በቻይና የኢትዮጵያ አምባሳደር ተሾመ ቶጋ ተናገሩ፡፡

አምባሳደሩ በኢትዮጵያ በሰሜኑ አካባቢ ያለውን ወቅታዊ ሁኔታ አስመልክተው  ለቻይና ጋዜጠኞች ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

በመግለጫቸውም መንግሥት የዜጎችን ደኅንነት፣ የአገሪቱን ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነት ለማስጠበቅ ሲል ተገዶና ጥቃት ተከፍቶበት ወደ ጦርነት መግባቱን ገልጸዋል።

ችግሩን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት መንግሥት ያለውን  ቁርጠኝነት በተግባር ማሳየቱንና አሁንም በአቋሙ ጸንቶ መቆየቱን አክለዋል።

ጎን ለጎንም የመከላከያ ሠራዊት በሚወስዳቸው እጅግ ጥንቃቄ የተሞላባቸው እርምጃዎች በአሁኑ ወቅት የትግራይ ክልል ከተሞችን እየተቆጣጠረ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ሠራዊቱ ሰላማዊ  ዜጎችን ሰለባ ላለማድረግ በከተሞች ላይ ውጊያን ባለማድረግ ስልታዊ በሆነ መንገድ ቁልፍ ሥፍራዎችን መቆጣጠር ተችሏል ነው ያሉት።

ሠራዊቱ በያዛቸው ከተሞችና አንዳንድ ሥፍራዎች መሰረተ-ልማቶችን ዳግም ለማስጀመር እንቅስቃሴ መጀመሩን አስረድተዋል።

የሰብዓዊ ድጋፎችም እየተጠናከሩ መሆኑን አንስተው በዚህ ረገድ ቻይና ጨምሮ ሌሎች አገራትም የበኩላቸውን ድጋፍ እንዲያደርጉ መንግሥት ጥሪ ማቅረቡን ገልጸዋል።  

በሌላ በኩል በኢትዮጵያና በቻይና መካከል ያለውን ምጣኔ ኃብታዊና ፖለቲካዊ አጋርነትና የባለብዙ ወገን ዲፕሎማሲያዊ ትብብራቸውን  ለማጠናከር በትኩረት እየተሰራ መሆኑን አምባሳደሩ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም