ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ የዓለም አቀፉ የትምህርት ትብብር ተቋም ዋና መቀመጫ ልትሆን ነው

ጥቅምት 15/2015 (ኢዜአ) ኢትዮጵያ በደቡባዊ የዓለም ክፍል የሚገኙ አገራት የዓለም አቀፉ የትምህርት ትብብር ተቋም(ኦኢሲ) ዋና መቀመጫ እንደምትሆን ተገለጸ።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የትምህርት፣የሳይንስና የባህል ድርጅት(ዩኔስኮ) የኢትዮጵያ ዳይሬክተር ዶክተር ሪታ ቢሶናውት እና የኦኢሲ ዋና ፀሐፊ ሼክ መንሱር ሙሳላምን ዛሬ በጽህፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ከሼክ መንሱር ጋር በነበራቸው ውይይት ዓለም አቀፍ የትምህርት ትብብር ተቋም ዋና መቀመጫውን ኢትዮጵያ እንድትሆን መምረጡን አድንቀው የኢትዮጵያ መንግስት ለተቋሙ አስፈላጊውን ድጋፍ ሁሉ እንደሚያደርግ ገልጸዋል።

የኦኢሲ ዋና ፀሐፊ ሼክ መንሱር ሙሳላም በበኩላቸው ኢትዮጵያ ተቋሙን ዋና መቀመጫ ለማድረግ መወሰኗ እንዳስደሰታቸውና በዚህም ኢትዮጵያ ዘርፉ ብዙ ጠቀሜታ ታገኛለች ብለዋል።

መንግስት ለተቋሙ ስራዎች ስኬታማነት ድጋፍ ለማድረግ ላሳየው ቁርጠኝነትም ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

የዓለም አቀፉ የትምህርት ትብብር ተቋም(ኢኦሲ) እ.አ.አ. በ2000 በላቲን አሜሪካ ፣ካሪቢያን፣እስያ፣ አፍሪካ፣በመካከለኛው ምስራቅና ፓሲፊክ ደሴት በሚገኙ አገራት የተቋቋመ የበይነ መንግስታት ድርጅት ነው።

የተቋሙ ዋንኛ አላማ ፍትሐዊና ሁሉን አቀፍ የትምህርት ተደራሽነት በማስፈን በአገራቱ ዘላቂ የሰው ሃብት፣ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ልማት እንዲሰፍን ማድረግ ነው።

ኢኦሲ ከዚህ ቀደም ዋና መቀመጫ ቢሮውን በኢትዮጵያ ለመክፈት እንደሚፈልግ በተደጋጋሚ ሲገልጽ መቆየቱ ይታወቃል።

በሌላ በኩል ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ከዩኔስኮ የኢትዮጵያ ዳይሬክተር ዶክተር ሪታ ቢሶናውት ጋር ተወያይተዋል።

አቶ ደመቀ ዩኔስኮ የኢትዮጵያ ቅርሶች ጥበቃና ክብካቤን ለመጠበቅ በገንዘብና በቴክኒክ እያደረገ ያለውን ድጋፍ አድንቀዋል።

ዶክተር ሪታ በበኩላቸው ሁለቱ ወገኖች ትምህርት፣ባህልና ሳይንስን በማስተዋወቅ ረገድ ያላቸውን ትብብር ማጠናከር እንደሚገባቸው መግለጻቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም