በኢትዮጵያ የባንክ ዘርፍ የውጭ ባለሀብቶች እንዲገቡ የህግና የመመሪያ ማሻሻያዎች እየተደረጉ ነው-ብሔራዊ ባንክ - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮጵያ የባንክ ዘርፍ የውጭ ባለሀብቶች እንዲገቡ የህግና የመመሪያ ማሻሻያዎች እየተደረጉ ነው-ብሔራዊ ባንክ
ጥቅምት 15/2015 /ኢዜአ/ በኢትዮጵያ የባንክ ዘርፉ ለውጭ ባለሀብቶች ክፍት እንዲሆን መወሰኑን ተከትሎ የህግና የመመሪያ ማሻሻያዎች እየተደረጉ መሆኑን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ አስታወቀ።
ይህን ተከትሎም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በፖሊሲ እና የባንክ አዋጅ ማሻሻያ ረቂቅ ላይ ከባንኮች፣ ከኢንሹራንስ ኩባንያዎች፣ ከማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት አድርጓል።
በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የፋይናንስ ተቋማት ሱፐርቪዥን ምክትል ገዥ ሰለሞን ደስታ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ የባንክ አገልግሎት ለውጪ ገበያ የተፈቀደው የኢኮኖሚ ዕድገትን ለማፋጠን፣ የውጪ ምንዛሬን ለማግኘት እና ኢኮኖሚውን ለማነቃቃት ነው።
በመሆኑም ወደ ህግና ፖሊሲ ትግበራ ከመገባቱ በፊት ከሀገር ውስጥ የዘርፉ ባለድርሻዎች ጋር በመወያየት ግብዓቶችን መሰብሰብ ማስፈለጉን ጠቅሰዋል።
የተለያዩ አገራትን ልምድ በመውሰድ ባንኮች ስራቸውን መጀመር በሚችሉባቸው ሁኔታዎች ላይም የዝግጅት ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ጠቅሰዋል።
ለአብነትም የባንክ አዋጅ ማሻሻያ እየተደረገ መሆኑን ጠቅሰው፤ የተለያዩ መመሪያዎችም በዝግጅት ሂደት ላይ መሆናቸውን አክለዋል።
የውጭ ባንኮች ወደ ኢትዮጵያ ሲመጡ ለኢኮኖሚው እንዲሁም ለቴክኖሎጂ እውቀት ሽግግር የራሳቸውን ሚና እንደሚያበረክቱ ተናግረዋል።
በውይይቱ የተሳተፉ የባንክና ኢንሹራንስ አመራሮች በበኩላቸው የውጭ ሀገራት ባንኮች በኢትዮጵያ ስራ ሲጀምሩ ሊከሰቱ የሚችሉ ችግሮችን በጥንቃቄ ማየት እንደሚገባ ተናግረዋል።
የውጭ ባንኮች ካፒታላቸውን በሀገር ውስጥ በማስመዝገብ ብሔራዊ ባንክ ቁጥጥር የሚያደርግበት አሰራር መዘርጋት አለበትም ነው ያሉት።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ምክትል ገዥ ሰለሞን ደስታ በበኩላቸው ባንኩ ሊከሰቱ የሚችሉ ችግሮችን መቅረፍ የሚያስችለውን አሰራር እያዘጋጀ ነው ብለዋል።
ከውጭ የሚገቡ ባንኮች ወደ ስራ ሲገቡ እነሱን ለመቆጣጠር የሚቻልበት የህግ አግባብ መኖሩን ጠቅሰው፤ አሰራሩን የሚጥሱ ከሆነም በህጉ መሰረት እንደሚጠየቁ ተናግረዋል።