ቀጥታ፡

ኢትዮጵያና ጅቡቲ የምጣኔ ሃብትና የዲፕሎማሲ ትብብራቸውን ወደላቀ ደረጃ ለማሸጋገር እየሰሩ ነው

ጥቅምት 15 ቀን 2015 (ኢዜአ) ኢትዮጵያና ጅቡቲ የምጣኔ ሀብትና የዲፕሎማሲ ትብብራቸውን ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር እየሰሩ መሆኑን የሀገራቱ ከፍተኛ ዲፕሎማቶች ገለጹ።

16ኛው የኢትዮ-ጅቡቲ የሚኒስትሮች የጋራ ኮሚሽን ስብሰባ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው።

ሁለቱ ሀገራት የሚያጋጥሟቸውን ችግሮች በጋራ በመፍታት የምጣኔ ሃብት፣ የፖለቲካና የህዝብ ለህዝብ ግንኙነታቸውን አጠናክረው ለማስቀጠል ቁርጠኛ መሆናቸውን በስብሰባው መክፈቻ ላይ የአገራቱ ዲፕሎማቶች አረጋግጠዋል።

በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአፍሪካ ጉዳዮች ጄነራል ዳሬክተር አምባሳደር ፍስሃ ሻወል ኢትዮጵያ የሁለቱን ሀገራት የጋራ ተጠቃሚነት በሚያረጋግጡ ጉዳዮች ላይ ትብብሯን አጠናክራ ትቀጥላለች ብለዋል።

በየዓመቱ የሚካሄደው የኢትዮ-ጅቡቲ የሚኒስትሮች የጋራ ኮሚሽን ስብሰባ እየዳበረ የመጣውን የሁለትዮሽ ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር እያገዘ መሆኑን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያና ጅቡቲ በአህጉር፣ ክፍለ አህጉርና ዓለም አቀፍ መድረኮች ላይ በትብብር አቋማቸውን እያራማዱ እንደሆነ ተናግረዋል።

የጋራ ስብሰባውም የንግድ፣ የሰላምና ጸጥታ እንዲሁም የህዝብ ለህዝብ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቶች የሁለቱን ሀገራት ጥቅም ባስከበረ መልኩ በተሳለጠ ሁኔታ እንዲከናወኑ ያግዛል ነው ያሉት።

ኢትዮጵያ በምስራቅ አፍሪካ የምጣኔ ሃብት ውህደት እንዲመጣ በትኩረት እየሰራች መሆኗንም አምባሳደር ፍስሐ ተናግረዋል።

ለዚህም ከጅቡቲ ጋር ያላት የባቡር፣ የኤሌክትሪክ ኃይል፣ የመንገድ፣ የወደብና የንግድ ትስስር ተጨባጭ ማሳያ መሆኑን ጠቅሰዋል።

የጅቡቲ ሉኡካን ቡድን መሪ አምባሳደር መሃዲን ኦብሲህ በበኩላቸው ጅቡቲና ኢትዮጵያ ከባህልና ቋንቋ ግንኙነት ባለፈ በብዙ የትብብር መስኮች ጠንካራ ወዳጅነት እንዳላቸው አውስተዋል።

በተለይም በዓለም የዲፕሎማሲ ትብብር ውስጥ እንደ ምሳሌ ሊጠቀስ የሚችል የምጣኔ ሃብት ትብብር በሁለቱ አገሮች መካከል መፈጠሩንም በመግለጽ።

ስብሰባው ዛሬን ጨምሮ ለቀጣዮቹ አራት ቀናት የሚካሄድ ሲሆን ሁለቱ አገሮች በሰላምና ጸጥታ፣ ንግድ፣ ግብርና፣ ወደብ፣ የባቡር ትራንስፖርትና ሌሎች ጉዳዮች ላይ ትብብራቸውን የበለጠ በሚያጠናክሩባቸው ጉዳዮች ላይ የሀገራቱ የየዘርፉ ተወካዮች እየተወያዩ ነው።

በውይይታቸው ያሉ መልካም እድሎችና እያጋጠሙ ያሉ ችግሮችን ከነመፍትሔዎቻቸው በጋራ ስብሰባው የመዝጊያ መርሃ-ግብር ላይ የሁለቱ ሀገራት ሚኒስትሮች የሚያቀርቡ ይሆናል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም