መከላከያ ሠራዊት በወሰደው ርምጃ የሽብር ቡድኑ ታጣቂዎች በሁሉም ግንባር እጅ እየሰጡና እየተበተኑ ነው - ኢዜአ አማርኛ
መከላከያ ሠራዊት በወሰደው ርምጃ የሽብር ቡድኑ ታጣቂዎች በሁሉም ግንባር እጅ እየሰጡና እየተበተኑ ነው
ጥቅምት 15 ቀን 2015 (ኢዜአ) መከላከያ ሠራዊት በወሰደው ርምጃ የሽብር ቡድኑ ታጣቂዎች በሁሉም ግንባር እጅ እየሰጡና እየተበተኑ መሆኑ ተገለፀ።
የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት በወሰደው ከባድና ፈጣን ርምጃ የሕወሐት ታጣቂዎች መበተናቸውንና እጅ መስጠታቸው ተገልጿል።
ሌሎች ደግሞ በተሳሳተ መረጃ ተደናግረው ምን ማድረግ እንዳለባቸው ግራ እንደተጋቡ መረጃዎች አመልክተዋል።
በቅርቡ ለመከላከያ እጅ የሰጡ የአሸባሪው ሕወሓት ታጣቂዎች የክፋት አዝማቾቻቸውን ሁኔታ በአንድ ጥሩ የትግርኛ ምሳሌያዊ አነጋገር ገልጸውታል።
"ማሽላውን ከአደጋ ለመከላከል የከበበው አጥር ለማሽላው እንጂ ራሱ አጥሩን አልጠቀመውም" ይሄም የአሸባሪው መሪዎች እንጂ ታጣቂዎቹ ከጦርነቱ ያተረፉት እልቂት ብቻ መሆኑን እንደሚያሳይ ተመላክቷል።
በመሆኑም የተበተኑና ከቡድኑ የጥፋት ወጥመድ ማምለጥ የሚፈልጉ ታጣቂዎች መከላከያ ወደ ተቆጣጠራቸው የትግራይ አካባቢዎችና ወደ አጎራባች ክልሎች በመሄድ እጃቸውን በሰላም እንዲሰጡ የመከላከያ ሠራዊት ጥሪ ያቀርባል።
እጃቸውን ለሚሰጡ የቡድኑ ታጣቂዎች አስፈላጊው ክብካቤ እንዲደረግ መመሪያ ተላልፏል።
የአጎራባች ክልሎችና ከህወሓት የተላቀቁ የትግራይ አካባቢዎች ሕዝብ፣ እጅ የሚሰጡ የቡድኑ ታጣቂዎችን በመቀበል፣ ተንከባክቦ ለመከላከያ ሠራዊቱ እንዲያስረክብ መከላከያ መልእክት ያስተላልፍላችኋል።