ቀጥታ፡

የሀገር መከላከያ ሠራዊት ከጀግንነቱ ባሻገር በሳይንስና ቴክኖሎጂ ኢትዮጵያን ወደፊት ለማራመድ መስራት አለበት- ዶክተር ሙላቱ ተሾመ

ጥቅምት 15 ቀን 2015 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ከጀግንነቱ ባሻገር በሳይንስና ቴክኖሎጂ ኢትዮጵያን ወደፊት ለማራመድ የሚያስችሉ ተግባራትን ማከናወን እንዳለበት የቀድሞው የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ ገለፁ።

የመከላከያ ሠራዊት ቀን ዛሬ ጥቅምት 15 ቀን 2015 ዓ.ም በተለያዩ ዝግጅቶች ተከብሮ ውሏል።

በመከላከያ ሠራዊት ጠቅላይ መምሪያ በተዘጋጀው መርሃ-ግብር ላይ የቀድሞ የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ ታድመዋል።

በዓለም ላይ የበርካታ ረቂቅና ውስብስብ ቴክኖሎጂ ግኝቶች ምንጭ መከላከያ እንደሆነ ገልጸው፤ የኢትዮጵያ መከላከያም ሀገሩን በቴክኖሎጂ ፈጠራ ማሻገር አለበት ብለዋል።

የሠራዊቱ ወደር የሌለው ጀግንነት በሳይንስና ቴክኖሎጂ፣ በሕዋ ሳይንስና በአየር ኃይል ቴክኖሎጂ ምርምሮች ጭምር መደገፉ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ነው ያሉት።

በዕለቱ የሰሜን ዕዝ ጥቃትና የመከላከያ ሠራዊት አገር የማዳን ተልዕኮን የሚዘክረው መጽሐፍ ለንባብ መብቃቱ የሚደነቅ መሆኑን ጠቅሰዋል።

የመከላከያ ሚኒስትር ዴኤታ ማርታ ሉዊጂ፤ የሀገር መከላከያ ሠራዊት የሀገር መከታና ኩራት መሆን በሚያስችል መልኩ በአስተማማኝ ሁኔታ መገንባቱን ገልጸዋል።

ለአገር ሉዓላዊነት የሚያደርገውን ተጋድሎና ድል በሁሉም መስኮች በመድገም የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ ልማት ለማረጋገጥ ሠራዊቱ ከመቼውም ጊዜ በላይ ዝግጁ መሆኑንም ተናግረዋል።

የመከላከያ ቀንን ስናከብር የሠራዊቱን ተጋድሎና ጀግንነት እየዘከርን ሌላ ደማቅ ታሪክ ለመፃፍ እየተዘጋጀን መሆን አለበት ሲሉም ገልጸዋል።

ለአገር ሰላም፣ ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነት በጀግንነት ዋጋ እየከፈለ ያለው የሀገር መከላከያ ሠራዊት በዚሁ ዓላማው ግቡን ለማሳካት ዝግጁ መሆኑን አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም