ቀጥታ፡

'የእሳት ቀለበት፤ የሕግ ማስከበር ዘመቻ ንፍቀ መዋዕል' መፅሐፍ በደም የተፃፈ የኢትዮጵያ ታሪክ ነው- የመፅሐፉ ሀያሲያን

ጥቅምት 15/2015 (ኢዜአ) 'የእሳት ቀለበት፤ የሕግ ማስከበር ዘመቻ ንፍቀ መዋዕል' በሚል የተዘጋጀው መፅሐፍ አገር የማዳን ታሪክ የሰነደና በደም የተፃፈ የኢትዮጵያ ታሪክ መሆኑን የመፅሐፉ ሀያሲዎች ገለጹ።

የመከላከያ ሰራዊት ቀን በተለያዩ ዝግጅቶች ተከብሮ በዋለበት በዛሬው ዕለት 'የእሳት ቀለበት፤ የሕግ ማስከበር ዘመቻ ንፍቀ መዋዕል' የተሰኘው የሰሜን ዕዝ መጠቃትና የሰራዊቱን ተጋድሎ የሚዳስስ መፅሐፍ ተመርቋል።

የቀድሞው ፕሬዚዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ፣ የመከላከያ ሚኒስትር ዴኤታ ማርታ ሉዊጂ፣ የመከላከያ ሰራዊት ከፍተኛ አመራሮችና አባላት፣ የቀድሞ ጦር አባላትና ሌሎችም እንግዶች በተገኙበት ተመርቋል።

በመከላከያ ጠቅላይ መምሪያ ባለቤትነት በተለያዩ አዘጋጆች የተፃፈው መፅሐፉ በሶስት ምዕራፎች ተዋቅሮ 360 ገፆች ያሉት ነው።  

አሁን ለህትመት የበቃው መፅሐፍ የመጀመሪያው ቅፅ ሲሆን ቀጣይ ሁለት ቅፆች የሚታተሙ መሆኑም ተገልጿል።

በመፅሐፉ ዙሪያ ዳሰሳ ካደረጉት መካከል ረዳት ፕሮፌሰር አበባው አያሌው 'የእሳት ቀለበት' የተሰኘው መፅሐፍ የያዘው ታሪክ በደም የተፃፈ ታሪክ ነው ብለዋል።

የመፅሐፍ ዳራ በተመለከተ የአሸባሪው የሕወሃት ቡድን ድርጊት በኢትዮጵያም በሌላም ዓለም እንዳልተፈፀመ ገልፀው፤ መፅሐፉ የህወሓትን ከደደቢት ጥንስስ ጀምሮ የነበረውን ፀረ-ኢትዮጵያ ታሪክ በጥሩ ሀተታ እንዳቀረበ ተናግረዋል።

ያለምንጭ ታሪክ እንደማይፃፍ ገልፀው፣ 'የእሳት ቀለበትም' የድርጊቱ ተሳታፊ የመጀመሪያ ደረጃ ምንጮችን የተጠቀመና በወቅቱ የተፃፈ በመሆኑ ከታሪክ መፅሐፍ አኳያ ጠንካራ ጎኑ እንደሆነ ጠቅሰዋል።

በይዘት ደረጃም በጥሩ ሀተታና ቋንቋ ከሞላ ጎደል የሕግ ማስከበር ዘመቻውን ሂደትና የጦርነቱ ተዋናዮች እንደተካተቱ ገልፀው ምናልባትም የደጀኑ ህዝብ አስተዋጽኦ ተካትቶበት ቢሆን የሚል ሃሳብም ሰንዝረዋል።

ሌላው የመፅሐፍ ዳሰሳ ያቀረቡት በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የጋዜጠኝነትና ተግባቦት መምህሩ ረዳት ፕሮፌሰር መኩሪያ መካሻ፤ መፅሐፉ ኢትዮጵያን የማዳን ታሪክ የሰነደ መፅሐፍ እንደሆነ ተናግረዋል።

መፅሐፉ ስለሰራዊቱ ድል ምስጢር፣ ስለ ህወሓት መርዘኝነት እንዲሁም ከጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም የሰሜን ዕዝ ጥቃትና ሰራዊቱ የእሳቱን ቀለበት በጥሶ አገር ያዳነበትን ታሪክ የሰነደ እንደሆነ አብራርተዋል።

የመከላከያ ሰራዊት አባላትን የአገር ፍቅር፣ የሞራል ብቃትና ጀግንነት እንዲሁም በእሳት የተፈተኑ የጦር መኮንኖች እንዳሉን የሚያስረዳ እንደሆነም አብራርተዋል።

'የእሳት ቀለበት፤ የሕግ ማስከበር ዘመቻ ንፍቀ መዋዕል' በሚል የተዘጋጀው መፅሐፍ አገር የማዳን ታሪክ የሰነደና በደም የተፃፈ የኢትዮጵያ ታሪክ መሆኑን ነው ሃያሲያኑ የተናገሩት።

የሁነቱ ተሳታፊዎች በሰጡት አስተያየትም የሰራዊቱ ተጋድሎ የሚዘክረው 'የእሳት ቀለበት' ሰራዊቱ የተፈጸመበትን ግፍና የባንዳዎችን ዕኩይ ታሪክ ለትውልድ የሚያስተለልፍ በመሆኑ ተደራሽ ፋይዳውን ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም