ቀጥታ፡

የፖለቲካና የሀሳብ ልዩነት ሳይገድበን ለሀገር ክብርና ሉዓላዊነት በአንድነት እንቆማለን- የፖለቲካ ፓርቲዎች

ሚዛን አማን ጥቅምት 15/2015 (ኢዜአ) ኢትዮጵያን ለማጽናት የፖለቲካና የሀሳብ ልዩነቶች ሳይገድበን ለሀገር ክብርና ሉዓላዊነት በአንድነት እንቆማለን ሲሉ የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች ገለጹ።

ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉት የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች የአመለካከትና የሀሳብ ልዩነቶችን በውይይት በማጥበብ ለኢትዮጵያ የተሻለ ነገን ለመፍጠር የበኩላቸውን እንደሚወጡ ተናግረዋል።

የኢዜማ ፓርቲ የቤንች ሸኮ እና ሸካ ዞን ማስተባበሪያ ምክር ቤት ሰብሳቢ ክፍሌ ሽፈራው እንዳሉት ጀግኖች አባቶች የፖለቲካና ሃይማኖት ልዩነት ሳያስቡ በአድዋ ጦርነት ኢትዮጵያን ከነክብሯ አቆይተዋል።

"ዛሬም ከኢትዮጵያ ህልውና ስለማይበልጥ በልዩነት ውስጥ ህብረትን ፈጥረን ስለአንዲት ኢትዮጵያ ክብር መቆም አለብን" ብለዋል።

"አሸባሪው ህወሓት በስልጣን ዘመኑ ህዝቡን በዘር ከፋፍሎ ለውጭ ጠላቶች ጫና ምቹ ሁኔታ ቢፈጥርም በአለት ላይ የቆመውን ኢትዮጵያዊነት ማፍረስ አይቻልም" ነው ያሉት።

የተለያዩ አመለካከቶችና የሀሳብ ልዩነቶች ቢኖሩም በኢትዮጵያ ጉዳይ አንድ ሆነን በጋራ የመታገል ሃላፊነት አለብን" ሲሉ አመልክትዋል።

በብልጽግና ፓርቲ የቤንች ሸኮ ዞን ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ዮናስ ኬና በበኩላቸው "በታሪካችን በአንድነት የደም ዋጋ ከፍለን ኢትዮጵያን ከእነ ክብሯ ያቆምን ህዝቦች ነን፣ የውጭ ጠላት የሀገር ውስጥ ባንዳዎችን ተጠቅሞ የከፈተውን የእጅ አዙር ጦርነት በመቀልበስ ታሪክ እንደግማለን" ብለዋል።

ህወሓት እያካሄደ ያለው የውክልና ጦርነት እንዳይቀጥል የውስጥ አንድነትንና ለሀገር መከላከያ ሠራዊት የሚደረገውን ድጋፍ ማጠናከር እንደሚገባም አመልክተዋል።

የተረጋጋ የፖለቲካ ሥርዓት በመዘርጋትና የጥፋት ድግሶችን ለማክሰምና ኢትዮጵያን ከፍ ለማድረግ በጋራ መቆም እንደሚገባም ተናግረዋል።

"ሀገር ከሌለች ስልጣን መያዝም ሆነ ህዝብ መምራት ስለማይቻል ቅድሚያ ለሀገር ህልውና እንሰጣለን" ያሉት ደግሞ በቤንች ሸኮ ዞን የእናት ፓርቲ ተወካይ አቶ ተክለማርያም አይሻ ናቸው።

"አሸባሪው ህወሓት በስልጣን ዘመኑ የዘረጋውን የዘረኝነት ፖለቲካ በመቀልበስ ህዝቦች በኢትዮጵያዊነት መንፈስ ተዋደውና ተከባብረው እንዲኖሩ ለማድረግ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሚናችን የጎላ በመሆኑ ለእዚህ እንሰራለን" ብለዋል።

የፖለቲካ ልዩነቶችን በመደማመጥ መስመር አስይዞ በጋራ ከተሰራ የኢትዮጵያ ዕድገት ሩቅ እንደማይሆንም ተናግረዋል።

በተለይ ለውጭ ሃይሎች መግቢያ በር ሊሆኑ የሚችሉ የራሳችንን የውስጥ ጉዳዮች ተነጋግረን በራሳችን መፍታት አለብን ያሉት አቶ ተክለማርያም፣ በእዚህም አሸባሪው ህወሓትና ጋላቢዎቹ ኢትዮጵያን ለመበትን ያላቸውን ጭፍን ፍላጎት ማክሸፍ እንደሚቻል አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም