ወጣቱ የጀግና ሰራዊቱን ፈለግ በመከተል ለሀገር መጽናት የድርሻውን ሊያበረክት ይገባል-የምዕራብ እዝ መምሪያ - ኢዜአ አማርኛ
ወጣቱ የጀግና ሰራዊቱን ፈለግ በመከተል ለሀገር መጽናት የድርሻውን ሊያበረክት ይገባል-የምዕራብ እዝ መምሪያ
ጎንደር ጥቅምት 15/2015(ኢዜአ) ወጣቱ ትውልድ ለሀገሩ ክብርና ለዜጎች ነፃነት የሚዋደቀውን ጀግና ሰራዊት ፈለግ በመከተል ለሀገር መጽናት የድርሻውን ሊያበረክት እንደሚገባ የምዕራብ እዝ መምሪያ አመለከተ፡፡
በየዓመቱ ጥቅምት 15ቀን የሚከበረው "የመከላከያ ሰራዊት ቀን" በጎንደር ከተማ በሚገኙ ትምህርት ቤቶች በተለያዩ ዝግጅቶች በድምቀት ተከብሯል፡፡
የምዕራብ እዝ መምሪያ ተወካይ ሌተናል ኮሎኔል ታደለ ዳኘው በፋሲለደስ አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተገኝተው ባስተላለፉት መልዕክት ኢትዮጵያ በየዘመኑ ጀግኖች የሚፈልቁባት የኩሩ ህዝቦች ሀገር ናት ብለዋል፡፡
አሁን ላይም የውጭ ጠላቶችና የውስጥ ባንዳዎች በቅንጅት አገር ለማፍረስ የከፈቱትን ጦርነትጀግናውመከላከያሰራዊት በመመከት አኩሪ ድል እያስመዘገበ ይገኛል ሲሉ ገልጸዋል።
“ወጣቱ ትውልድም የጀግናው ሰራዊታችን የጀግንነት ታሪክ በማስቀጠል ከውስጥና ከውጪ የሚነሱ ታሪካዊ ጠላቶችን አይቀጡ ቅጣት በመቅጣት ሰላም ለማስፈን ቁርጠኛ ሆኖ መንቀሳቀስ አለበት” ብለዋል።
የኢትዮጵያ የሰራዊት ቀን መከበር የጀመረው በዳግማዊ አጼ ሚኒሊክ በ1900 ዓም መሆኑን ጠቁመው ይህም ክብረ በዓል “በአገራችን ሚንስቴር ተቋቁሞ በአዋጅ የራሷን ዘመናዊ ሠራዊት የመሰረተችበትን ታሪካዊ እለት ለማስታወስ ያለመ ነው” ብለዋል፡፡
ሀገር ታፍራና ተከብራ እስካሁን የዘለቀችው በሰራዊቱ ጽኑ ተጋድሎ መሆኑን የገለጹት ደግሞ የፋሲለደስ አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርእሰ መምህር እንዳለ ታደሰ ናቸው፡፡
ለሀገሩ ውድ ህይወቱን እየሰጠ ለሚገኘው የመከላከያ ሰራዊት ትውልዱ ትልቅ አክብሮት ሊሰጥ እንደሚገባ ጠቁመው የሰራዊቱን ታሪክ መዘከር እንደሚገባ ተናግረዋል።
“አባቴ የመከላከያ ሰራዊት አባል በመሆኑ ታላቅ ኩራትና ክብር ይሰማኛል” ያለችው ተማሪ ቃልኪዳን አብዬ ዛሬ በትምህርት ገበታ ላይ ለመገኘት የበቃነው በሰራዊታችን ተጋድሎና የህይወት መስዋእትነት በመሆኑ ከጠላት ጋር እየተዋደቁ ለሚገኙ ለአባቴና ጓደኞቹ ምስጋናዬ የላቀ ነው” ስትል ገልጻለች፡፡