ከደጀኑ ህዝባችን ጋር ሆነን የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት እያስከበርን በልማትም የከፍታ ጉዞዋን ለማሳካት ዝግጁዎች ነን - ኢዜአ አማርኛ
ከደጀኑ ህዝባችን ጋር ሆነን የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት እያስከበርን በልማትም የከፍታ ጉዞዋን ለማሳካት ዝግጁዎች ነን
ጥቅምት 15/2015/ኢዜአ/ ከደጀኑ ህዝባችን ጋር ሆነን የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት እያስከበርን በልማትም የከፍታ ጉዞዋን ለማሳካት ዝግጁዎች ነን ሲሉ የሀገር መከላከያ ሰራዊት አባላት ተናገሩ።
የመከላከያ ሰራዊት ቀን መከበር የተሰጠንን ተልዕኮ በብቃት ለመፈጸም ያለንን ዝግጁነት የበለጠ የሚጨምር ነው ብለዋል።
ለኢትዮጵያ ሉዓላዊነት መስዋእትነት እየከፈለ ያለውን ሰራዊት ለማመስገን እና ለማበረታታት የመከላከያ ሰራዊት ቀን "የጥንካሬያችን ምንጭ ህዝባችን ነው” በሚል መሪ ቃል በተለያዩ ዝግጅቶች እየተከበረ ነው።
ዕለቱ ጉልህ ታሪክ ጽፈው ያለፉ ጀግኖች ሰማዕታትን በመዘከር ሰራዊቱ ሁለንተናዊ ዝግጅት የሚያደርግበት እና ተልዕኮ የመፈጸም ብቃቱን የሚያሳይበት ነው።
የሀገር መከላከያ ሰራዊት ሀገራዊ ፍቅሩን፣ የመለዮ ክብሩን እንዲሁም የእርስ በእርስ ግንኙነቱን አጠናክሮ በማደስ ዳግም ቃልኪዳን የሚገባበት እለት መሆኑም ተነግሯል።
ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉ የሰራዊቱ አባላት እንዳሉት የሰራዊት ቀን ሲከበር በተለያዩ ግንባሮች ግዳጁን እየተወጣ ያለውን ሰራዊት በማሰብ ሊሆን ይገባል።
በባህር ኃይል የሰው ሀብት ልማትና አስተዳደር ዳይሬክተር ኮሎኔል ተዘራ በቀለ፤ በዓሉ ሲከበር ያለፈ ታሪካችንን እየዘከርን ለቀጣይ ተልዕኮ ዝግጁ መሆናችንን በመግለጽ ነው ብለዋል።
በዓሉ ሲከበርም ሰራዊቱ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት የማስከበር ተልዕኮውን በላቀ ብቃት በመወጣትና ህዝቡም በየተሰማራበት መስክ ሀገርን በሚያሻግሩ ተግባራት ላይ በትኩረት በመስራት ሊሆን እንደሚገባ ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ አየር ኃይል የከባድ ጥገና ማእከል ሎጂስቲክስ ኃላፊ ሻለቃ ገመቹ በቀለ በበኩላቸው የሰራዊት ቀን መከበር የታሪካችን አንዱ አካል ነው ይላሉ።
በዓሉ ሰራዊቱ ኢትዮጵያን ከብዙ ውጫዊና ውስጣዊ ፈተናዎች እያሻገረ ባለበት ወቅት መከበሩም የተለየ ስሜት የሚፈጥር መሆኑን ጠቁመዋል።
የበዓሉን ዓላማ በመረዳት በየግንባሩ መስዋእትነት እየከፈሉ ያሉ የሰራዊቱን አባላት በማሰብና ተልዕኮን በመወጣት ማክበር እንደሚገባም ነው የጠቀሱት።
ለዚህም ከደጀኑ ህዝባችን ጋር ሆነን የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት እያስከበርን የከፍታ ጉዞዋን ለማሳካት ሁልጊዜም ዝግጁዎች ነን ብለዋል።
የመከላከያ ሰራዊት ቀን የሚከበርበት ዕለት ታሪክን ያማከለ ነው ያሉት በመከላከያ ጥናትና ምርምር ማእከል የወታደራዊ ንድፈ ሀሳብ ጥናት ዳይሬክተር ኮሎኔል ሙላት ደሳለኝ ናቸው።
ሰራዊት የኢትዮጵያና የህዝቧ ዘብ እንጂ ከየትኛውም የፖለቲካ ስርዓት ጋር ወገንተኛ አለመሆኑ በደንብ ሊታወቅ እንደሚገባ ገልጸዋል።