ተጠባቂው የቅዱስ ጊዮርጊስና ፋሲል ከነማ የፕሪሚየር ሊግ ጨዋታ - ኢዜአ አማርኛ
ተጠባቂው የቅዱስ ጊዮርጊስና ፋሲል ከነማ የፕሪሚየር ሊግ ጨዋታ
ጥቅምት 15/ 2015 (ኢዜአ) በቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የአምስተኛ ሳምንት መርሐግብር ተጠባቂ የሆነው የቅዱስ ጊዮርጊስና ፋሲል ከነማ ጨዋታ ዛሬ ይደረጋል።
ዛሬ በፕሪሚየር ሊጉ ሁለት ጨዋታዎች ይደረጋሉ።
ቅዱስ ጊዮርጊስ ከፋሲል ከነማ ከቀኑ 10 የሚያደርጉት ጨዋታ በጉጉት ይጠበቃል።
ፈረሰኞቹ ፕሪሚየር ሊጉን በ12 ነጥብ እየመሩ ነው፤ በአንጻሩ በአፍሪካ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ የማጣሪያ ጨዋታዎች ምክንያት ሁለት ተስተካካይ ጨዋታ የሚቀራቸው አፄዎቹ በሶስት ነጥብ 14ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል።
ቅዱስ ጊዮርጊስ በ2014 ዓ.ም ከአምስት ዓመት ቆይታ በኋላ የፕሪሚየር ሊጉን ዋንጫ ለ15ኛ ጊዜ ያነሳ ሲሆን፤ፋሲል ከነማ በ2013 ዓ.ም የሊጉ አሸናፊ እንደነበር አይዘነጋም።
ቅዱስ ጊዮርጊስና ፋሲል ከነማ ዛሬ የሚያደርጉት ጨዋታ በፕሪሚየር ሊጉ 12ኛው የእርስ በእርስ ግንኙነታቸው ነው።
ፋሲል ከነማ አምስት ጊዜ ሲያሸንፍ ቅዱስ ጊዮርጊስ አራት ጊዜ አሸንፏል፤በተቀሩት ሁለት ጨዋታዎች አቻ ተለያይተዋል።
በግንኙነታቸው ቅዱስ ጊዮርጊስ 15 ፋሲል ከነማ ደግሞ 12 ግቦችን አስቆጥረዋል።
የፈረሰኞቹና የአፄዎቹ ደጋፊዎች ለጨዋታው ድምቀት ይሆናሉ ተብሎ ይጠበቃል።
ኢንተርናሽናል አርቢትር አሸብር ሰቦቃ የሁለቱን ክለቦች ጨዋታ በመሐል ዳኝነት ይመሩታል።
ኢንተርናሽናል አርቢትሩ በ2014 ዓ.ም ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ሁለተኛ ዙር ፋሲል ከነማ ቅዱስ ጊዮርጊስን 1 ለ 0 ያሸነፈበትን ጨዋታ መምራታቸው የሚታወስ ነው።
በሌላ የፕሪሚየር ሊጉ የአምስተኛ ሳምንት ጨዋታ ወልቂጤ ከተማ ከሲዳማ ቡና ከቀኑ 7 ሰአት ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።
ትናንት በፕሪሚየር ሊጉ የአምስተኛ ሳምንት የመጀመሪያ ቀን ጨዋታዎች ኢትዮ ኤሌትሪክ ከአዳማ ከተማ እንዲሁም ሐዋሳ ከተማ ከድሬዳዋ ከተማ በተመሳሳይ ሁለት አቻ በሆነ ውጤት ተጠናቋል።