ቀጥታ፡

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት 21ኛውን ክፍለ ዘመን የሚመጥን ማሻሻያ ማድረግ ይኖርበታል- የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር

ጥቅምት 15 2015 (ኢዜአ) የተባበሩት መንግስታት ድርጅት (ተመድ) 21ኛውን ክፍለ ዘመን የሚመጥን ማሻሻያ ማድረግ እንደሚያስፈልገው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ።

የዓለም አቀፍ የባለብዙ ወገን ዲፕሎማሲ ፍትሐዊና አሳታፊ ሊሆን ይገባዋል ብሏል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ትናንት የተከበረውን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ቀን አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ የተመድ መስራች አባል የሆነችው ኢትዮጵያ እ.አ.አ 1945 በስራ ላይ የዋለው የድርጅቱ ቻርተር ጽንሰ ሀሳቦች ተፈጻሚነት በቁርጠኝነት እየሰራች መሆኑን ገልጿል።

ለዓለም ሰላምና የጋራ ደህንነት ካላት ጉልህ አስተዋጽኦ አኳያም የኢትዮጵያ ሴቶችና ወንዶች ከእ.አ.አ 1950ዎቹ መጀመሪያ አንስቶ የተመድ የሰላም ማስከበር ተልዕኮዎች ጠንካራ ሚና መጫወት መቀጠሏን አመልክቷል።

ኢትዮጵያ ከ60 ዓመት በላይ የተመድ የአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽን መቀመጫ በመሆኗ ኩራትና ክብር ይሰማታል ነው ያለው ሚኒስቴሩ በመግለጫው።

የዓለም አቀፍ የባለብዙ ወገን ዲፕሎማሲ ለሰዎች አንገብጋቢ ፈተናዎች የተሻለ ምላሽ ለመስጠት ሁሉን አቀፍ፣ አሳታፊ፣ ፍትሐዊና ወካይ ሊሆን እንደሚገባው ገልጿል።

የባለብዙ መስረክ አሳታፊነት ከተመድ ቻርተር ምሰሶዎች ጋር የተጣጣመ መሆን እንዳለበትም አመልክቷል።

ኢትዮጵያ በተመድ ቻርተር እና መሰረታዊ ጽንሰ ሀሳቦቹ ያሉ የባለብዙ ወገን መርሆዎች እያከበረበች በምትገኝበት ወቅት የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ለ21ኛው ክፍለ ዘመን የሚመጥን የተሻሻለ፣ ብቁ እና ሊተገበር የሚችል ማሻሻያዎችን እንዲያደርግ ጥሪ ታቀርባለች ሲል የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም