ቀጥታ፡

ለኢትዮጵያ ክብርና ሉአላዊነት በጀግንነት ለተዋደቁ የሰራዊት አባላት ቋሚ መታሰቢያ ሊኖር ይገባል-ብርጋዴር ጀነራል ካሳዬ ጨመዳ

ጥቅምት 15 ቀን 2015 (ኢዜአ) ለኢትዮጵያ ክብርና ሉአላዊነት በጀግንነት ለተዋደቁ የሰራዊት አባላት ቋሚ መታሰቢያ ሊኖር እንደሚገባ የቀድሞ የሀገር መከላከያ ሰራዊት ከፍተኛ የጦር መኮንን ብርጋዴር ጀነራል ካሳዬ ጨመዳ ገለጹ።

የሀገር መከላከያ ሰራዊት ቀንን በማስመልከት በመከላከያ ጠቅላይ መምሪያ የተዘጋጀና ከጥቅምት 14 እስከ 18 ቀን 2015 ዓ.ም የሚቆይ የፎቶ ግራፍ አውደ ርዕይ በመከላከያ ሚኒስቴር ዋና መስሪያ ቤት በይፋ ተከፍቷል።

በአውደ ርዕዩ መክፈቻና ጉብኝት ላይ የተገኙት የቀድሞ የሀገር መከላከያ ሰራዊት ከፍተኛ መኮንን ብርጋዴር ጄነራል ካሳዬ ጨመዳ ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ እንዲህ አይነት ዝግጅቶች ብሔራዊ መግባባትን ለመፍጠር ከፍተኛ ትርጉም አላቸው።

የኢትዮጵያ ሰራዊት በአጼ ምንሊክ ዘመነ መንግስት በአግባቡ ስለመደራጀቱ ከታሪክ መረዳታቸውን አስታውሰው፤ በአጼ ምንሊክ የተደራጀው ጦር በዓለም አቀፍ ደረጃ እውቅና ኖሮት በተለያዩ መገናኛ ብዙሃን ሽፋን ያገኘ እንደነበርም ገልጸዋል።

በመሆኑም አሁን ላይ የሰራዊት ቀን ታሪክን መነሻ አድርጎ በመከበር ላይ በመሆኑ ለአገሩ እየተዋደቀ ላለው ሰራዊትና ለሁላችንም ደስታን የፈጠረ ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ለማስጠበቅ ሰራዊቱ በየትኛውም አጋጣሚ በጀግንነት መስዋእትነት በመክፈል ላይ መሆኑን ጠቅሰው፤ ለኢትዮጵያ ክብርና ሉዓላዊነት በጀግንነት ለተዋደቁ የሰራዊት አባላት ቋሚ መታሰቢያ ሊኖራቸው ይገባል ብለዋል።

የሰራዊቱ የጀግንነት ታሪክ በመንግስት ወይም በሰዎች መለዋወጥ የማይናወጥ ሆኖ በቋሚነት የሚወሳ ክብርና እውቅና ሊሰጠው ይገባልም ነው ያሉት ጀነራሉ።

የአገር መከላከያ ሰራዊት የሚከፍለው መስዋእትነት ለኢትዮጵያ ክብርና ሉዓላዊነት በመሆኑ ዘመን የማይሽረው አኩሪ ገድል መሆኑንም ገልጸዋል።

ብርጋዴር ጄነራል ካሳዬ ጨመዳ፤ ከመስመራዊ መኮንንነት እስከ ከፍተኛ መኮንንነት ሰራዊቱንና አገራቸውን ያገለገሉ ታላቅ ባለውለታ መሆናቸው ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም