ጂቡቲ ከኢትዮጵያ ስንዴ የመግዛት ፍላጎት እንዳላት ገለጸች - ኢዜአ አማርኛ
ጂቡቲ ከኢትዮጵያ ስንዴ የመግዛት ፍላጎት እንዳላት ገለጸች
ጥቅምት 15/2015/ኢዜአ/ ኢትዮጵያ ስንዴ ወደ ውጭ ገበያ መላክ ስትጀምር ጂቡቲ የመግዛት ፍላጎት ያላት መሆኑን የሀገሪቱ የግብርና ሚኒስትር መሀመድ አህመድ አዋሌህ ገለጹ።
ኢትዮጵያና ጂቡቲ ጠንካራ ጉርብትና እና ረጅም ዘመን ያስቆጠረ ወዳጅነት ያላቸው ሀገራት ናቸው።
ሁለቱ ሀገራት በመሪዎች ደረጃ፣ በህዝብ ለህዝብ፣ በምጣኔ ሃብት እንዲሁም በቀጣናዊና ዓለምአቀፋዊ መስኮች ጠንካራ ትብብር ያላቸው መሆኑም ይታወቃል።
በኢትዮ ጂቡቲ የባቡር መስመር፣ በታዳሽ ኃይል፣ መሰረተ ልማት፣ በየብስ መንገድ፣ በገቢና ወጪ ንግድ ቀጣናዊ ውህደትን ለመፍጠር የተጀመረውን ጉዞ ሀገራቱ አጠናክረው ቀጥለዋል።
የጂቡቲ የግብርና ሚኒስትር መሀመድ አህመድ አዋሌህ በተለይ ለኢዜአ እንደገለጹት ኢትዮጵያ ለጂቡቲ በግብርናው ዘርፍ የፍራፍሬ ምርትና የንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦትን በማመቻቸት ከፍተኛ ሚና አላት።
በአሁኑ ወቅት ደግሞ የምግብ ዋስትናንናን ለማረጋገጥና የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል በጀመረችው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር መሰረት ለጂቡቲ ለምግብነትና ለደን ልማት የሚውሉ ችግኞችን መለገሷን ጠቅሰዋል።
ሚኒስትሩ አክለውም ኢትዮጵያ ከጀመረችው የስንዴ ልማት ብዙ ተሞክሮ እንደምትወስድ ገልጸው፤ ኢትዮጵያ ስንዴ ወደ ውጭ ገበያ ማቅረብ ስትጀምር ጂቡቲ የምትገዛ መሆኑን ተናግረዋል።
በቀጣይ የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት በተለይ በድንበር ተሻጋሪ የግብርና ልማት ለማጠናከር እንሰራለን ሲሉም አረጋግጠዋል።
ኢትዮጵያ ቀጣናዊ የኢኮኖሚ ውህደትን ለመፍጠርና ጠንካራ አካባቢን እውን ለማድረግ የተለያዩ ተግባራትን እያከናወነች ትገኛለች።
ለአብነትም በመንገድና በኃይል መሰረተ ልማት ዘርፍ ከቀጣናው ሀገራት ጋር ጠንካራ ትስስር እየፈጠረች ሲሆን የህዝብ ለህዝብ ግንኙነትንም ከመቼውም ጊዜ በላይ ትኩረት ሰጥታዋለች።
ቀጣናው ያለበትን የምግብ ዋሰትና ስጋት እንዲቀርፍና ከርዳታ ጥገኝነት እንዲላቀቅም በበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ለሌሎች ተሞክሮ የሚሆን ስኬታማ ስራ እያከናወነች መሆኑ ይታወቃል።
የአረንጓዴ ዲፕሎማሲንም በቀጣናዊ ደረጃ የጀመረች ሲሆን አህጉራዊ ለማድረግ እየተንቀሳቀሰች ትገኛለች።