የግብርና ምርታማነትን የሚያሳድጉ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ እንደሚገባ ተጠቆመ - ኢዜአ አማርኛ
የግብርና ምርታማነትን የሚያሳድጉ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ እንደሚገባ ተጠቆመ
ጥቅምት 14 ቀን 2015 (ኢዜአ) የግብርና ምርታማነትን የሚያሳድጉ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀምና የግብርናውን ዘርፍ በማዘመን የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ እንደሚገባ ተጠቆመ፡፡
የዓለም የምግብ ቀን "ሁሉን አቀፍ የተሻለ ምርት፣ የተሻለ አመጋገብ፣ የተሻለ አካባቢ እና የተሻለ ህይወት" በሚል መሪ ሀሳብ በሀገር አቀፍ ደረጃ በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ሸዋ ዞን ሉሜ ወረዳ በተለያዩ መርሃ ግብሮች ተከብሯል፡፡
በዓሉ በሉሜ ወረዳ የተለያዩ ቀበሌዎች የሚገኙ የአቮካዶ፣ የስንዴ እና የጤፍ ክላስተርን በመጎብኘት እና በፓናል ውይይት ነው የተከበረው፡፡
በዚሁ ወቅት እንደተገለጸውም የዜጎችን የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ ግብርናን ማዘመን፣ ቴክኖሎጂዎችን እና ከፍተኛ ምርት መስጠት የሚያሥችሉ ግብዓቶችን መጠቀም ይገባል፡፡
በዓለም የምግብና እርሻ ድርጅት (ፋኦ) የኢትዮጵያ ተወካይ ፋራዪ ዚሙድዚ፣ የዜጎችን የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ መንግስት፣ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርግቶችና የግሉ ሴክተር በቅንጅት እንዲሰሩ ጠይቀዋል፡፡
ፋኦ አገራት የምግብ ዋስትናቸውን እንዲያረገግጡ የተለያዩ ድጋፎችን በማድረግ ላይ መሆኑን ጠቁመው፣ ይህንኑም አጠናክሮ እንደሚቀጥል ነው የተናገሩት።
በዓለም አቀፍ ደረጃ በርካታ አምራቾች ቢኖሩም ዛሬም ድረስ የምግብ ዋስትናን ሙሉ ለሙሉ መረጋገጥ አልተቻለም ብለዋል፡፡
በተለይ በማደግ ላይ ባሉ አገራት የግብርና ቴክኖሎጂዎች አጠቃቀም ባለመስፋፋቱና በተለያዩ ሰው ሰራሽና ተፈጥሯዊ አደጋዎች ችግሩ የከፋ መሆኑን ነው የገለጹት፡፡
በቀጣይ የግብርናውን ክፍለ ኢኮኖሚ መደገፍ አስፈላጊ መሆንን ገልጸው፣ ለዚህም ድርጅታቸው ከባለድርሻ አካላት ጋር እንደሚሰራም አረጋግጠዋል፡፡
በዓለም የምግብ ፕሮግራም የኢትዮጵያ ዳይሬክተር ክላውድ ጂቢዳር በበኩላቸው፣ የዓለም የምግብ ቀን ሲከበር ርሃብን ማጥፋት ላይ ትኩረት ሊደረግ ይገባል ብለዋል፡፡
የዓለም ምግብ ፕሮግራምም ከእጅ ወደ አፍ የሆነ የግብርና ኑሮ ላይ የሚገኙ አርሶ አደሮች ራሳቸውን በምግብ እንዲችሉ ለመደገፍ ቁርጠኛ ነው ሲሉም ገልጸዋል፡፡
የግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ማንደፍሮ ንጉሴ ኢትዮጵያ ለራስዋ ብቻ ሳይሆን የምግብ ችግር ላለባቸው አገራት ጭምር እያመረተች ነው ብለዋል፡፡
የኦሮሚያ ክልል ግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ አበራ ወርቁ በበኩላቸው በኦሮሚያ ክልል የክለስተር እርሻን ተግባራዊ በማድረግ ምርትና ምርታማነት እንዲጨምር እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
በዚህም የስንዴ፣ የገብስ፣ የቡና እና የአቮካዶ እንዲሁም ሌሎችን ምርቶች በክላስተር በማምረት ለክልሉ እና ለአገሪቱ ኢኮኖሚ አስተጽኦ በማድረግ ላይ መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡
በበዓሉ አከባበር ላይ የገንዘብ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ሳማሪታ ሰዋሰው፣ የኦሮሚያ ክልል ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎችን ጨምሮ ሌሎችም ተሳትፈዋል።
በሉሜ ወረዳ በመጪው የበጋ ወራት 20 ሺህ ሄክታር መሬት በበጋ መስኖ ስንዴ ለማልማት እቅድ መያዙን ከወረዳው ግብርና ፅህፈት ቤት የተገኘው መረጃ ያሳያል።