ቀጥታ፡

ውጤታማ የሰብል ዝርያዎች ተደራሽ የማድረግ ስራዎች ስኬታማ እንዲሆኑ በትጋት ይሰራል -አቶ ኡሞድ ኡጁሉ

ጋምቤላ ጥቅምት 14/2015 (ኢዜአ ) ውጤታማ የሰብል ዝርያዎች ተደራሽ በማድረግ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የተጀመሩ ስራዎች ስኬታማ እንዲሆኑ ባለድርሻ አካላት በትጋት ሊሰሩ እንደሚገባ የጋምቤላ ክልል ርዕሰ-መስተዳድር አቶ ኡሞድ ኡጁሉ አስገነዘቡ።

በክልሉ በአቦቦ ወረዳ  ‘‘አርዲ’’ እና ‘‘ቦሰት’’ በተባሉ የስንዴና የጤፍ ዝርያዎች ለመጀመሪያ ጊዜ የተካሄደ የሰብል ልማትን ጎብኝተዋል። 

ርዕሰ መስተዳድሩ በአንድ ባለሃብት የለማ የስንዴና የጤፍ ሰብልን በጎበኙበት ወቅት እንዳሉት ውጤታማ የግብርና ቴክኖሎጂዎችን ለአርሶ አደሩ ተደራሽ በማድረግ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የዘርፉ አመራሮችና ባለሙያዎች በትኩረት ሊሰሩ ይገባል።

በክልሉ ተሞክረው የማይታወቁ የስንዴና የጤፍ ሰብሎች ውጤታማ መሆናቸው የክልሉ መሬት ከተሰራበት የማይቀበለው የሰብል ዓይነት እንደሌለ በመስክ ምልከታው ማረጋገጣቸውን ተናግረዋል።

በክልሉ በስንዴና በጤፍ ሰብል ልማት ባለሃብቶች የጀመሩትን ተግባር አጠናከረው መቀጠል እንዳለባቸው ጠቁመው የክልሉ መንግስት በዘርፉ ለተጀመሩ የልማት ስራዎች ስኬታማነት ሁለንተናዊ ድጋፉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል።

በክልሉ ለመጀመሪያ ጊዜ የስንዴና የጤፍ ሰብሎችን ውጤታማ በሆነ መልኩ አልምቶ በተግባር ላሳየው ለፍሬ ህይወት ከተማ የእርሻ ልማት ድርጅት ምስጋና በማቅረብ ሌሎችም ባለሃብቶች በዚህ ዓይነት ልማት እንዲሳተፉ ጠይቀዋል።

የክልሉ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ቢሮ ኃላፊ አቶ አጃክ ኡቻላ የስንዴ ሰብል ካሁን በፊት በሙከራ ደረጃ እንጂ በተጠቃሚዎች ዘንድ ለምቶ ያልታየ እንደነበር ተናግረዋል።

በተለይም የስንዴ ሰብል ከሙከራ አልፎ በተግባር ውጤታማ በሆነ መልኩ ለምቶ መታየቱን ጠቁመው "ዘንድሮ አርሶ አደሩንና ባለሃብቱን በማሳተፍ በስፋት ወደ ልማቱ ለመግባት እየተሰራ ነው" ብለዋል።

በክልሉ ግብርና ምርምር ተቋም በተካሄደ ሙከራ በተለይም ‘‘አርዲ’’ እና ‘‘ቦሰት’’ የተሰኙ የስንዴና የጤፍ ዝርያዎች ለአካባቢው ስነ-ምህዳር ተስማሚ ሰለመሆናቸው መረጋገጡን የክልሉ የስንዴ ልማት ግብረ ኃይል ጸሃፊና የግብርና ተመራማሪ ዶክተር ዮናስ ከፍያለው ገልጸዋል።

This image has an empty alt attribute; its file name is ጋምቤላ3.jpg

አርዲ የተሰኘው የዳቦ ስንዴ ያለ ምንም ማዳበሪያ በሄክታር 35 ኩንታል፣ እንዲሁም ቦሰት የተሰኘው የጤፍ ዝርያ ደግሞ 17 ኩንታል እንደሚሰጡ በሙከራ መረጋገጡን ተናግረዋል።

የክልሉ ስንዴ ልማት ግብረ-ሃይል በተያዘው በጀት ዓመት አርሶ አደሩንና ባለሃብቱን በማስተባበር ከ2 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በስንዴ ለማልማት እየሰራ መሆኑን አመለክተዋል ።

"የሩዝ ሰብል በክልሉ ውጤታማ ስለሆነ በትኩረት ይሰራል" ሲሉም አክለዋል።

የፍሬ ህይወት ከተማ የእርሻ ልማት ስራ አስኪያጅ አቶ ሰለሞን ጸጋዬ በበኩላቸው አርዲና ቦሰት የተሰኙ የስንዴና የጤፍ ዝርያዎች ድርቅንና በሽታን የሚቋቋሙ ዝርያዎች መሆናቸውን በተግባር ማረጋገጣቸውን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም