ኢትዮጵያውያን በአንድነት በመቆም ለጠላት እንደማይበገሩ በተግባር ያሳዩትን አቋም ሊያጠናክሩ ይገባል-ዶክተር ይልቃል ከፋለ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያውያን በአንድነት በመቆም ለጠላት እንደማይበገሩ በተግባር ያሳዩትን አቋም ሊያጠናክሩ ይገባል-ዶክተር ይልቃል ከፋለ
ባህር ዳር (ኢዜአ) ጥቅምት 14/2015 "ኢትዮጵያውያን በችግር ወቅት በአንድነት በመቆም ለጠላት እንደማይበገሩ ከመልዕክት ባለፈ በተግባር ያሳዩትን አቋም አጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል ሲሉ" የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ይልቃል ከፋለ ገለጹ።
"የትህነግ የአማራ ጥላቻና የፈጸመው የዘር ማጥፋት ወንጀል የምርምር ውጤት" በሚል ርዕስ የታተመ መጽሐፍ በባህር ዳር ከተማ ተመርቋል።
ርዕሰ መስተዳድሩ በእዚህ ወቅት እንደገለጹት ህዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) ሲመሰረት ጀምሮ የአማራን ህዝብ በጥላቻ ፈርጆ በርካታ ግፎችንና መከራዎችን ሲፈጽምበት ኖሯል።
ህወሓት በኢትዮጵያ ህዝብ ትግል ከስልጣን ከተባረረ በኋላ በኢትዮጵያ ህዝብ ሃብት በገዛው መሳሪያ ኢትዮጵያን እንደ ሀገር ለማፍረስ አልሞ ተደራራቢ ችግሮች ማድረሱን ነው ዶክተር ይልቃል የገለጹት።
"የሽብር ቡድኑ አገር ለማፍረስ በተደጋጋሚ የከፈተውን ጦርነት በመመከት የኢትዮጵያን ሉዓለዊነት ለማስከበር ሁሉም ኢትዮጵያዊያን በተግባር መስዋዕትነት ከፍለዋል" ብለዋል።
"በፖለቲካ አመለካከት ልዩነቶች ቢኖሩም አገር እንደ አሁኑ አደጋ ላይ ስትሆን ኢትዮጵያውያን ልዩነትን ትተው በጋራ በመቆም ለጠላት አይበገሬነታቸውን አሳይተዋል" ሲሉም ገልጽዋል።
የኢትዮጵያ ህዝብ ዛሬም ይህንን በተግባር እያስመሰከረ መሆኑን የጠቆሙት ዶክተር ይልቃል፣ በቀጣይም ይህ ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
የተመረቀው መጽሐፍ ከታተመ በኋላም አሸባሪው ህወሓት በርካታ ጉዳቶችን ማድረሱን ያስታወሱት ዶክተር ይልቃል፣ በቀጣይም የአሸባሪውን ቡድን የወንጀል ጥግና ጥፋቶቹን የሚያሳዩ መጻህፍት እንደሚጻፉ አመልክተዋል።
መጽሐፉ የአሸባሪው ህወሓት ቡድኑ በህዝብ ላይ ያደረሰውን አስነዋሪ ሰባዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ስነ-ልቦናዊ ጉዳት መጠን እንደሚያሳይም ዶክተር ይልቃል ጠቁመዋል።
መጽሐፉ ከሰኔ 2013 እስከ ታህሳስ 2014 ዓ.ም አሸባሪው ህወሓት በወረራ ይዟቸው በነበሩ አካባቢዎች ያደረሰውን ጉዳት ብቻ እንደሚያሳይ የገለጹት ደግሞ የጥናት ቡድኑ የቴክኒክ አስተባባሪና የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ መምህርና ተመራማሪ ዶክተር አዳነ ተስፋዬ ናቸው።
ዶክተር አዳነ እንዳሉት መጽሀፉ የተዘጋጀው በዩኒቨርሲቲ ምሁራን፣ በክልሉ የተለያዩ ቢሮዎች፣ በአማራ ክልል ማዕከላዊ ስታቲስቲክስ አገልግሎት እና በአማራ ምሁራን መማክርት ጉባኤ ትብብር ነው።
አሸባሪ ቡድኑ በፈፀመው ወረራ ከ291 ቢሊዮን 816 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ሃብት መውደሙን በጥናቱ ለማረጋገጥ እንደተቻለ በመጸሀፉ ተመላክቷል።
በመጽሐፉ የምረቃ ስነ-ስርዓት ላይ የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የህዝብ ተወካዮች አባላት፡ ምሁራንና ልዩ ልዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ተገኝተዋል ሲል የዘገበው ኢዜአ ነው።