የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር 5 ሺህ 150 አባወራዎችን ተጠቃሚ የሚያደርግ የ50 ሚሊዮን ብር ድጋፍ አደረገ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር 5 ሺህ 150 አባወራዎችን ተጠቃሚ የሚያደርግ የ50 ሚሊዮን ብር ድጋፍ አደረገ
ደብረ ብርሃን ጥቅምት 14/2015 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር 5 ሺህ 150 አባወራዎችን ተጠቃሚ የሚያደርግ የ50 ሚሊዮን ብር ድጋፍ ማድረጉን አስታወቀ።
ድጋፉ የተደረገው በደብረ ብርሃን ከተማ ጊዜያዊ መጠለያ ጣቢያ ለሚገኙ ወገኖች ሲሆን ድጋፉም በጥሬ ገንዘብ እንደተሰጠ ማህበሩ ገልጿል።
በኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር የሰሜን ሸዋ ቅርጫፍ ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ዳምጠው እምሻው እንዳሉት የገንዘብ ድጋፉ የተደረገው ከዓለም አቀፍ ቀይ መስቀል ማህበር ጋር በመተባበር ነው።
ማህበሩ ከዚህ በፊት ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለው በጊዜያዊ መጠለያ ጣቢያ ለሚገኙ ወገኖች ከ100 ሚሊየን ብር በላይ የሚያወጣ የምግብና ምግብ ነክ ያልሆኑ ቁሳቁሶችን መደገፉን አስታውሰዋል።
የጥሬ ገንዘብ ድጋፉ ተፈናቃይ ወገኖች የሚፈልጉትን ምግብና ምግብ ነክ ያልሆኑ ቁሳቁሶችን ገዝተው መጠቀም እንዲችሉ ለማገዝ የተደረገ መሆኑንም ተናግረዋል።
በዚሁ ድጋፍ 5 ሺህ 150 አባወራዎች ተጠቃሚ መሆናቸወን ጠቅሰው፤ ይህም የተፈናቃይ ወገኖችን ወቅታዊ ችግር ለማቃለል የተደረገ ነው ብለዋል።
ለተፈናቃይ ወገኖች ጊዜያዊ ችግራቸውን ከመጋራት አልፎ በዘላቂነት እንዲቋቋሙ የሚመለከተው ሁሉ መረባረብ እንዳለበት የገለጹት ሃላፊው፤ ማህበሩ በዚህ ረገድ እያደረገ ያለውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥልም አስታውቀዋል።
በድጋፉ ተጠቃሚ ከሆኑት መካከል አቶ ድጋፌ ሞገሴ እንዳሉት እስካሁን የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበርን ጨምሮ መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች እንዲሁም ግለሰቦች እያገዙን ይገኛሉ።
የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር በቤተሰባቸው ልክ የ14 ሺህ ብር ድጋፍ እንዳደረገላቸው ጠቅሰው፤ ይህም ጊዜያዊ ችግራቸውን ለማቃለል እንደሚያግዛቸው ተናግረዋል።
መንግስት የአካባቢውን ሰላምና ፀጥታ በማረጋገጥ ወደ ቀደመው ቀያቸው በመመለስ ሰርተው ሀብት የሚያፈሩበትና ከተረጅነት የሚወጡበትን ሁኔታ እንዲያመቻችላቸውም ጠይቀዋል።
ከምዕራብ ሸዋ ዞን ከመኖሪያ ቀያቸው ተፈናቅለው አምስት ቤተሰብ ይዘው እያስተዳደሩ እንደሆነ የተናገሩት ወይዘሮ ደመቁ እሸቱ በበኩላቸው ማህበሩ የ12 ሺህ ብር ድጋፍ እንዳደረገላቸው ገልፀዋል።