ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ለፕሬዚዳንት ሺ ጂንፒንግ የደስታ መልዕክት አስተላለፉ - ኢዜአ አማርኛ
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ለፕሬዚዳንት ሺ ጂንፒንግ የደስታ መልዕክት አስተላለፉ
ጥቅምት 14/2015 (ኢዜአ) ጠቅላይ ሚኒስትር እና የብልጽግና ፕሬዚዳንት ዐቢይ አሕመድ ለቻይናው ፕሬዚዳንት ሺ ጂፒንግ የቻይና ኮሙኒስት ፓርቲ ዋና ፀሀፊ ሆኖ መመረጣቸው ተከትሎ የደስታ እና የመልካም ምኞት መልዕክታቸው አስተላልፈዋል።
በአመራር ዘመናቸው የቻይናን ኢኮኖሚያዊ እድገትን ከማስቀጠል ባለፈ የሀገሪቱን ዓለም አቀፍ ተፅዕኖ ፈጣሪነትን በማሳደግ በኩል ትልቅ ሚና መጫወታቸውንም አንስተዋል።
በመልዕክታቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፣ አሁን ላይም ዓለም የቻይናን ኮሚዩኒስት ፓርቲ ሀገር በቀል የልማት ሞዴልን ጠቃሚነት እንደሚረዳ እምነቴ ነው ብለዋል ።
ኢኮኖሚያዊ እድገትን በማረጋገጥ እና በዜጎች መካከል ያለውን የኑሮ ልዩነት ለማጥበብ ያደረጉት ያልተቋረጠ ጥረትም እንደ ኢትዮጵያ ላሉ ታዳጊ ሀገራት ምርጥ ተሞክሮ ነው ሲሉ ገልጸዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳሉት፣ ኢትዮጵያ ከፓርቲው በርካታ ልምዶችን ቀስማለች በተለይም በሰው ተኮር ልማት፣ በውጤታማ አስተዳደር እንዲሁም በሕዝብ አገልግሎት አሰጣጥ ረገድ መልካም ተሞክሮ መውሰዷን አንስተዋል።
በእርስዎ አስተዳደር ቻይና የኢትዮጵያ ስትራቴጂካዊ አጋር ሀገር ናት ሲሉም ነው የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ።
በቀጣይም በተለያዩ ዘርፎች የሀገራቱን ሕዝቦች ጥቅም ባስከበረ መልኩ በትብብር እንደሚሰራ አመላክተዋል።