የአገልግሎት ክፍያዎችን በቴሌብር መፈፀም ጊዜና ጉልበትን የሚቆጥብና ያልተገቡ አሰራሮችን የሚያስቀር ነው-ሚኒስቴሩ - ኢዜአ አማርኛ
የአገልግሎት ክፍያዎችን በቴሌብር መፈፀም ጊዜና ጉልበትን የሚቆጥብና ያልተገቡ አሰራሮችን የሚያስቀር ነው-ሚኒስቴሩ

ጥቅምት 14 ቀን 2015 (ኢዜአ) የአገልግሎት ክፍያዎችን በቴሌብር መፈፀም ጊዜና ጉልበትን የሚቆጥብና ያልተገቡ አሰራሮችን የሚያስቀር መሆኑን የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ገለጸ።
የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር የአገልግሎት ክፍያዎችን በቴሌ ብር መፈጸም የሚያስችለውን ስምምነት ከኢትዮ ቴሌኮም ጋር ተፈራርሟል።

የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ገብረመስቀል ጫላ እና የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈጻሚ ፍሬህይወት ታምሩ ስምምነቱን ፈርመውታል።
ስምምነቱ ባለጉዳዮች ከአዲስ የንግድ ምዝገባ፣ ፈቃድ፣ ማሻሻያ እና ውል ማቋረጥን እንዲሁም ከንግድ ስያሜ፣ ጋር የተያያዙ ክፍያዎች በቴሌ ብር እንዲፈጽሙ ያስችላቸዋል።
የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትሩ ገብረመስቀል ጫላ፤ የንግዱ ማኅበረሰብ የአገልግሎት ክፍያዎችን በቴሌብር መፈፀሙ ከጊዜና ጉልበት ብክነት የሚገላግልና ያልተገቡ አሰራሮችን የሚያስቀር መሆኑን ገልጸዋል።
ከ38 ሺህ በላይ የንግዱ ማኅበረሰብ በቴሌ ብር ከ3 ሚሊዮን ብር በላይ ግብይት መፈጸሙ ትልቅ ስኬት መሆኑን ጠቅሰው፤ የሚኒስቴሩ አገልግሎቶችም በዚሁ ሲስተም መከናወኑ ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።
የቴሌብር አገልግሎት ከተጀመረ ወዲህ በኦንላይን የሚገለገለው የንግድ ማኀበረሰብ ክፍል እየጨመረ ነው ብለዋል።
የአገልግሎት ክፍያዎችን በቴሌብር ለመፈፀም ከኢትዮ ቴሌኮም ጋር የተደረሰው ስምምነት ዘርፈ-ብዙ ጠቀሜታ ያለው መሆኑን ገልጸው፤ በቀጣይም የመሰረታዊ ሸቀጦች ሥርጭትና ሌሎችም መስኮች ላይ ትብብራችን ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈጻሚ ፍሬህይወት ታምሩ በበኩላቸው፤ ከዓለም ጋር ለመራመድና የሚጠበቀውን እድገት ለማስመዝገብ ዲጂታል አሰራር ቅንጦት ሳይሆን መሰረታዊ ጉዳይ መሆኑን ተናግረዋል።
ኢትዮ ቴሌኮም የዲጂታል ኢኮኖሚን በመገንባት ሂደት ከተቋማት ጋር በመሆን አሻራውን እያሳረፈ መሆኑን ጠቁመው፤ የዛሬው ስምምነትም የዚሁ ተግባር አንዱ ማሳያ መሆኑን ገልጸዋል።
የመንግሥት አገልግሎቶች በተሻለ መልኩ ለሕብረተሰቡ ተደራሽ እንዲሆኑ የማድረጉን ሥራ ኢትዮ ቴሌኮም አጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
በኢትዮጵያ የቴሌብር አገልግሎት ተጠቃሚዎች 25 ሚሊዮን መድረሱንና አገልግሎቱን ለማሳለጥም ከ16 ባንኮች ጋር ትስስር መፍጠሩን አሰታውቀዋል።