የሀገር ፍቅር ቴአትር ቤት እድሳት መጠናቀቁን ተከትሎ ለሦስት ቀናት የሚቆይ የኪነ-ጥበብ ዝግጅት ይቀርባል-ቢሮው - ኢዜአ አማርኛ
የሀገር ፍቅር ቴአትር ቤት እድሳት መጠናቀቁን ተከትሎ ለሦስት ቀናት የሚቆይ የኪነ-ጥበብ ዝግጅት ይቀርባል-ቢሮው
ጥቅምት 14 ቀን 2015 (ኢዜአ) የሀገር ፍቅር ቴአትር ቤት እድሳት መጠናቀቁን ተከትሎ ለሦስት ቀናት የሚቆይ የኪነ-ጥበብ ዝግጅት የሚቀርብ መሆኑን የአዲስ አበባ ባህል ኪነ-ጥበባት ቱሪዝም ቢሮ አስታወቀ።
የሀገር ፍቅር ቴአትር ቤት የፋሽስት ጣሊያን ወራሪ ኃይል መስፋፋት ባሳሰባቸው ወጣቶች አማካኝነት የተቋቋመ ቀጥሎም በወረራው ምክንያት ከሀገራቸው ተሰደው ፈረንሳይ ይኖሩ የነበሩት መኮንን ሀብተወልድ ወደ ሀገራቸው ከተመለሱ በኋላ ግንቦት 4 ቀን 1935 ዓ.ም የሀገር ፍቅር ማኅበር የሚለውን ስያሜ ማውጣታቸው ይታወሳል።
የሀገር ፍቅር ቴአትር ቤት በ1948 ዓ.ም ተገንብቶ አሁን ያለውን ቅርፅ ለመያዝ ቢበቃም ባለፉት 20 ዓመታት ምንም ዓይነት ዕድሳትና ማሻሻያ ሳይደረግለት መቆየቱ ተጠቅሷል።
የአዲስ አበባ ባህል ኪነጥበባት ቱሪዝም ቢሮ በ2013 ዓ.ም ያስጀመረው የእድሳት ሥራ መጠናቀቁን አስመልክቶ በቴአትር ቤቱ መግለጫ ሰጥቷል።
በመግለጫውም ቴአትር ቤቱ ደረጃውን በጠበቀ ሁኔታ መታደሱን እና ለአገልግሎት ዝግጁ መሆኑን አስታውቋል።
የእድሳቱ መጠናቀቅን በማስመልከትም ከጥቅምት 18 እስከ 20 ቀን 2015 ዓ.ም ለሦስት ቀናት የሚቆይ የኪነ-ጥበብ ዝግጅት የሚቀርብ መሆኑን ቢሮው ገልጿል።
የቢሮው ኃላፊ ዶክተር ሂሩት ካሣው፤ ለኪነ-ጥበብ ዘርፉ በተሰጠው ትኩረት በመታገዝ እድሳቱ ቅድሚያ በማግኘት መከናወኑን ተናግረዋል።
ኪነ-ጥበብ በዓለም ዙሪያ ያለው ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ሚና ከፍተኛ በመሆኑ በተለይም ቴአትር ቤቶች በሚያቀርቡት ዝግጅት ትውልዱን እንዲገነቡ የሚረዱ ተግባራት እየተከናወኑ መሆናቸውን ጠቁመዋል።
የሀገር ፍቅር ቴአትር ቤት ዳይሬክተር አብዱልከሪም ጀማል፤ ቴአትር ቤቱ ለባለሙያውና ለተመልካች ምቹ ባለመሆኑ እድሳቱ አስፈላጊ እንደነበር አስታውሰው የእድሳት ስራው በጥሩ ሁኔታ እንደተጠናቀቀ ገልፀዋል።
የቴአትር ቤቱ እድሳት መጠናቀቁን ተከትሎም መደበኛ ትርኢቱን ከመስከረም 3 ቀን 2015 ዓ.ም ጀምሮ ማቅረብ መጀመሩን አስታውሰዋል።
አሁን ላይ ደግሞ ሂደቱን ለመላው የኪነ-ጥበብ ባለሙያ ለማስተዋወቅና በእድሳቱ ላይ ለተሳተፉ አካላት ዕውቅና የመስጠትና ለሦስት ቀናት የሚቆይ የተለያዩ ዝግጅቶች ይከናውናሉ ብለዋል።