በሰቆጣ፣ ላልይበላና ዋግኸምራ በጦርነቱ ሳቢያ ተቋርጦ የቆየውን የኤሌክትሪክ ኃይል ዳግም ለማስጀመር ጥገና ተጀመረ - ኢዜአ አማርኛ
በሰቆጣ፣ ላልይበላና ዋግኸምራ በጦርነቱ ሳቢያ ተቋርጦ የቆየውን የኤሌክትሪክ ኃይል ዳግም ለማስጀመር ጥገና ተጀመረ
ጥቅምት 14 ቀን 2015(ኢዜአ) በሰሜን ኢትዮጵያ በተካሄደው ጦርነት ጉዳት የደረሰበት የወልዲያ - አላማጣ የባለ 230 ኪሎ ቮልት የከፍተኛ ኃይል ማስተላለፊያ መሥመር ጥገና መጀመሩን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል አስታወቀ፡፡
የመስመሩ መጠገን ከዓመት በላይ ኃይል ተቋርጦባቸው የቆዩ የላልይበላና ሰቆጣ ከተሞች እንዲሁም ሌሎች የዋግኸምራ ዞን አካባቢዎች ኃይል እንዲያገኙ ያስችላል፡፡
በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የማስተላለፊያ መሥመሮችና ማከፋፈያ ጣቢያዎች የቴክኒክ ድጋፍ ኃላፊ አቶ ተስፋዬ መንግስቱ እንደገለፁት ከወልዲያ ዶሮግብር ማከፋፈያ ጣቢያ እስከ አላማጣ ማከፋፈያ ጣቢያ ድረስ በተደረገ ፍተሻ 50 ቦታዎች ላይ የኮንዳክተር ጉዳትና መበጣጠስ ተከስቷል፡፡
በአንድ ኃይል ተሸካሚ የብረት ምሰሶ ላይ በመሳሪያ የመመታት ጉዳት መድረሱንም ገልፀዋል፡፡
በአላማጣ ማከፋፈያ ጣቢያ በተደረገ ፍተሻ ጣቢያው ምንም ዓይነት ጉዳት እንዳልደረሰበትም ተረጋግጧል ነው ያሉት፡፡
አላማጣ ማከፋፈያ ጣቢያ ቀደም ሲል ከባህርዳር፣ አሸጎዳ እና ኮምቦልቻ ከተዘረጉ መስመሮች ኃይል ያገኝ እንደነበር የጠቀሱት ኃላፊው ከባህርዳር - አላማጣ የተዘረጋው የኃይል ማስተላለፊያ መሥመር እስኪጠገን ከኮምቦልቻ - አላማጣ ያለውን ባለ 230 ኪሎ ቮልት መሥመር የመጠገን ሥራ ተጀምሯል ብለዋል፡፡
ጥገናው ሲጠናቀቅ ከአላማጣ ማከፋፈያ ጣቢያ በ66 ኪሎ ቮልት ኃይል ሲያገኙ የነበሩት የላልይበላ፣ ሰቆጣና ማይጨው መስመሮች ዳግም ኃይል እንዲያገኙ ያስችላል ብለዋል።
በአካባቢው በተንቀሳቀሰው የጥገና ቡድን የሰው ኃይል በመጨመር የጥገናውን ስራ የማፋጠን ስራ በመከናወን ላይ መሆኑን ጠቁመዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ላለፉት ሁለት ዓመታት ኃይል የተቋረጠበት የወልቃይት ሁመራ አካባቢ ኃይል ማግኘት እንዲችል የደረሰውን ጉዳት መጠን የሚለይ የባለሙያዎች ቡድን ወደ ሥፍራው መንቀሳቀሱን አቶ ተስፋዬ አስታውቀዋል፡፡
በባለሙያዎቹ የጉዳት መጠን ሪፖርት ላይ ተመስርቶ የጥገና ሥራው የሚቀጥል መሆኑንም ተናግረዋል።
ከአሸባሪው ህወሓት ነጻ በወጡ አካባቢዎች የኤሌክትሪክ አገልግሎት ለማስጀመር በጥናት ላይ የተመሰረተ ስራ እየተሰራ መሆኑን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ቀደም ብሎ መግለጹ ይታወሳል።
አሸባሪው ህወሓት በኤሌክትሪክ መሰረተ ልማት ላይ በፈፀመው ጥቃት የትግራይና የአማራ አንዳንድ አካባቢዎች እስካሁን የኤሌክትሪክ ኃይል ማግኘት አልቻሉም።
ከአላማጣ እና ከሽሬ ሰብስቴሽን የኤሌክትሪክ ኃይል የሚያገኙ አካባቢዎች ለረጅም ጊዜ አገልግሎቱን አላገኙም።
ከአላማጣ ሰብስቴሽን የሚወጣውን ኃይል የሚጠቀሙ የላሊበላ፣ የሰቆጣና አብዛኛዎቹ የዋግህምራ ዞን ወረዳዎች የኤሌክትሪክ ኃይል እያገኙ አለመሆኑም ይታወቃል።