በቴሌ ብር የኦንላይን የንግድ ምዝገባና ፈቃድ አገልግሎት ተጀመረ - ኢዜአ አማርኛ
በቴሌ ብር የኦንላይን የንግድ ምዝገባና ፈቃድ አገልግሎት ተጀመረ

ጥቅምት 14/2015 (ኢዜአ) የቴሌ ብር አሰራርን በመጠቀም የኦንላይን ንግድ ምዝገባና ፈቃድ አገልግሎት ወደ ስራ መግባቱ ተገለጸ።
የአገልግሎቱ ማስጀመሪያ መርሐግብር እየተካሄደ ሲሆን አገልግሎቱን ለማስጀመር ኢትዮ ቴሌኮም ንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር በጋራ ሲሰሩ መቆየታቸው ተነግሯል።
ሚኒስትሩ አቶ ገብረመስቀል ጫላ እንደተናገሩት ለንግዱ ማህበረሰብ ቴሌብርን ተደራሽ ማድረግ የተቀላጠፈ አገልግሎት ለመስጠት ፋይዳው ከፍ ያለ ነው።
ዘርፉ ከዚህ ቀደም ለመልካም አስተዳደር ችግር ተጋላጭ ነበር ያሉት ሚኒስትሩ በቴሌ ብር አገልግሎት መሰጠቱ ችግሩን ለመቅረፍ ትልቅ አስተዋፅኦ ያበረክታል ብለዋል።
38 ሺህ የንግዱ ማህበረሰብ በቴሌ ብር እየተጠቀመ መሆኑን ጠቁመው ይህም ዘመናዊ አሰራርን በመከተል ረገድ አገራዊ ፋይዳ አለው በማለት አመልክተዋል።
የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ስራ አስፈጻሚ ፍሬህይወት ታምሩ በበኩላቸው ኢትዮ ቴሌኮም የመንግሥት አገልግሎት ወደ ዲጂታል እንዲቀየር የተለያዩ ስራዎችን እየሰራ ነው።
ከነዚህም ስራዎች መካከል ከንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ጋር የተደረገው ስምምነት አንዱ መሆኑን ጠቁመው በመሰረታዊ ምግብ ሸቀጦች ላይም ኢትዮ ቴሌኮም ከተቋሙ ጋር ይሰራል ብለዋል።