የዓለም አቀፍ የብዙኃን መገናኛዎች ሽፋን ጣልቃ ገብነትን ስለሚቃወመው ሰልፍ... - ኢዜአ አማርኛ
የዓለም አቀፍ የብዙኃን መገናኛዎች ሽፋን ጣልቃ ገብነትን ስለሚቃወመው ሰልፍ...
በመላው የአገሪቱ ከተሞች የተካሄዱት የምዕራባውያን ጣልቃ ገብነትና አሸባሪውን ህወሓት የሚያወግዙ ሰልፎች በበርካታ ዓለም አቀፍ የብዙኃን መገናኛዎች ሽፋን ማግኘት ችለዋል።
ከአሜሪካው የዜና ምንጭ አሶሼትድ ፕሬስ እስከ ቢቢሲ አማርኛ፣ ከቱርኩ አናዶሉ እስከ የአሜሪካ ድምጽ ራዲዮ፣ ከቲ.አር.ቲ ዎርልድ እስከ አል-ዐይን አማርኛ እንዲሁም ከአፍሪካ ኒውስ እስከ የሩሲያ ስፑቲኒክ እና የቻይናው ዥንዋ ሰልፎቹን በፎቶግራፍ እና በተንቀሳቃሽ ምስሎች ተደገፍው ሰፊ ሽፋን አግኝተዋል።
ቡሉምበርግ፣ ዴይሊ ሜይል፣ ኤቢሲ ኒውስ፣ የግብጽ ጋዜጦችን ጨምሮ በርካታ ዓለም አቀፍ የብዙኃን መገናኛዎች ደግሞ አሶሼትድ ፕሬስን ዋቢ አድርገው ስለተካሄዱት ሰልፎች በምስል የተደገፉ ሰፋፊ ዘገባዎችን ይዘው ወጥተዋል።
”ለኢትዮጵያ እቆማለሁ ድምጼን አሰማለሁ!” በሚል መሪ ቃል በመዲናይቱ አዲስ አበባ እና በተለያዩ የአገሪቱ ከተሞች በተካሄዱት ሰልፎች ላይ ሚሊዮኖች ኢትዮጵያውያን መሳተፋቸውን በዘገባቸው አካተዋል።
ሰልፈኞቹ “ለኢትዮጵያ ሥጋት ለዓለም ስጋት ነው” እና “የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ይከበር” የሚሉ በሰለፈኞቹ የተያዙት መፈክሮች የዓለም አቀፍ ብዙኃን መገናኛዎችን ትኩረት የሳበ ነበር።
ብዙኃን መገናኛዎቹ ምን አሉ፣ ምንስ አነሱ የሚለውን በጥቂቱ ለማሳየት በሚከተለው መልኩ ለማየት ተሞክሯል።
የቱርኩ አናዶሉ የዜና ምንጭ የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ ጃንጥራር አባይ በመዲናዋ በተካሄደው ግዙፍ ሰልፍ ላይ ያደረጉትን ንግግር በዘገባው ይዞ ወጥቷል።
“የውጭ ሀገራት በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ መግባታቸውን አቁመው አማፂ ሃይሎችን በተለይም አሸባሪውን ህወሓት እና አጋሮቹን ከመርዳት ሊቆጠቡ ይገባል” ማለታቸውን የዜና ምንጩ አትቷል።
“ኢትዮጵያውያን መንግሥትን የደገፈ እና ምዕራባውያንን ያወገዘ ሰልፍ አካሄዱ“ ሲል የዘገበው ደግሞ መቀመጫውን ፓሪስ ያደረገው አፍሪካ ኒውስ ነው።
አዲስ አበባ በተካሄደው የድጋፍ ሰልፍ የታደመችው ሰላማዊት በሪሁንን ያናገረው አፍሪካ ኒውስ ለምዕራቡ ዓለም ማስተላለፍ የፈለገችውን መልዕክት ይዞ ወጥቷል። "የማንም ጣልቃገብነት አንፈልግም፤ ሀገራችንን በራሳችን ሉዓላዊነት ማስተዳደር እንችላለን" ማለቷን በመጥቀስ።
የአሜሪካው የዜና ምንጭ የሆነው አሶሼትድ ፕሬስ በበኩሉ በተለያዩ የኢትዮጵያ ከተሞች በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በሀገሪቱ የውስጥ ጉዳይ የውጭ አካላት ጣልቃ ገብነትን በመቃወም ሰልፍ ማካሄዳቸውን በስፋት ዘግቧል።
አሸባሪው ህወሓትን በመቃወም እና በውስጥ ጉዳይ የውጭ አካላት ጣልቃ ገብነት በመቃወም በርካታ ኢትዮጵያውያን ወደ አደባበይ እና ወደ ጎዳናዎች ወጥተዋል ብሏል።
የምዕራባውያንን ጣልቃ ገብነትን በመቃወም በሳምንቱ መጨረሻ ኢትዮጵያውያን በዋሽንግተን ዲሲ እና አዲስ አበባን ጨምሮ በሁሉም የአገሪቱ ከተሞች ሰልፎች ማካሄዳቸውን የዘገበው ደግሞ የሩሲያ ስፑቲንክ ነው።
ቲ.አር.ቲ ዎርልድ የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ ጃንጥራራ አባይን ጠቅሶ እንዳለው በኢትዮጵያ አንድነት ላይ የሚደርሰውን ማንኛውንም ስጋት እና ጣልቃ ገብነት የኢትዮጵያ ህዝብና መንግሥት ይቃወማሉ፤ ጣልቃ የገቡ ሀገራትም ከድርጊታቸው እንዲተቃቡ መጠየቃቸውን አስፍሯል።
የቻይናው የዜና አገልገሎት ዢንዋ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን በተለያዩ የአገሪቷ ከተሞች የውጭ ጣልቃ ገብነት እና ጫናዎችን በማውገዝ ሰልፍ አካሂደዋል ነው ያለው።
ሰልፈኞቹ "ለኢትዮጵያ ስጋት ለዓለም ስጋት ነው" እና "ሉዓላዊነታችን ይከበር" የሚሉ መፈክሮችን በማንሳት ወደ አደባባዮች መውጣታቸውን አስነብቧል።
ኢትዮጵያውያን ያካሂዱት ሰልፍ ተወደደም ተጠላም በዓለም አቀፍ የብዙሃን መገናኛዎች ሰፊ ሽፋን ማግኘቱ የሚሳየው ነገር መኖሩን አያጠራጥርም። ምዕራባውያን አፍሪካን አስመልክተው የሚከተሉት የውጭ ፖሊሲ ዳግም የሚያጤኑበት ግዜ አሁን መሆኑን ነው።
ምዕራባውያን በአፍሪካ አገራት የውስጥ ጉዳይ ልክ እንደጓሯቸው ዘው ብለው ገብተው የሚፈተፍቱት እና የሚወስኑት ነገር ማቆሚያ ሊኖረው እንደሚገባ ሰፊው የኢትዮጵያ ህዝብ ቅዳሜ ዕለት ያደረገው ሰልፍ ማንቂያ ደወል ይሆናቸዋል።
ምዕራባውያን የሚዲያ ኢንዱስትሪዎች ለዘመናት የዓለምን የሃሳብ እና የአስተያየቶች ልዕልና (Monopoly of Ideas and Opinion) ይዘው ቆይተዋል። ምዕራባውያን ሚዲያዎች የዓለምን ዜናዎች ሲቆጣጠሩ ዘመናት ተቆጥረዋል። ቅኝታቸውም እንደ አፍሪካ ላሉ ሀገራት ግድ የሌለውና በትብብር መንፈስ የተገራ አለመሆኑ ደግሞ ሌላው አሳሳቢ ጉዳይ ነው። ይህ ደግሞ የምዕራባውያን የውጭ ፖሊሲን በቀሪው ዓለም ላይ ለመጫን ለዓመታት በመሣሪያነት አገልግሏል።
በገንዘብ እና በቴክኖሎጂ አቅማቸው የዳበሩት የምዕራቡ ዓለም ግዙፍ የሚዲያ ኩባንያዎች ስለዓለም የሚነግሩን በእነሱ እይታና ፍላጎት ብቻ ነው። ለዚህ ማሳያ እንዲሆን የጄምስ ሚቺራ መጽሃፍን ዳሰስ አርጎ ማለፍ ይጠቀማል። ጄምስ ሚቺራ በምዕራቡ ሚዲያ የአፍሪካ ምስሎች (Images of Africa in the Western Media) ለህትመት ባበቃው መጽሃፉ ኒው ዮርክ ታይምስ መቼ ይሆን የሚሊዮኖች አፍሪካውያን ህይወት አደጋ ላይ የሚጥል ድርቅና ረሃብ ሲከሰት ዜና አድርጎ በፊት ገጽ የሚያወጣው ሲል ይጠይቃል። ጄምስ ሚቺራ ሩቅ መሄድ ሳያስፈልገው ”እንስሳት ሲሞቱ” ሲል መልሷል።
ጄምስ ሚቺራ እንዲህ እንዲል ያደረገው እ.ኤ.አ. በ1992 ኒው ዮርክ ታይምስ አንዳንድ የምስራቅ እና ደቡብ አፍሪካ ሀገራት ድርቅ ያደረሰውን ረሃብ አስመልክቶ በስምንት ቀናት ውስጥ አምስት ዘገባዎችን ይዞ መውጣቱን ተከትሎ ነበር። የሚገርመው ግን ኒው ዮርክ ታይምስ ከዘገባቸው ታሪኮቹ ውስጥ ሦስቱ በጣም ጎልቶ የታዩ ሲሆን እነሱም ስለ ዝሆኖች፣ አውራሪስ እና ሌሎች ሊጠፉ ስለሚችሉ ዝርያዎች የሚያወሱ ነበሩ።
ስለ አፍሪካውያን ህይወት ግድ የሌላቸው ምዕራባውያን የአፍሪካ ሀዝቦች በራሳቸው ጉዳይ “እኔ አውቅልሃለሁ” ሲባሉ መስማት በአርግጥም ያማል። ጠቅለል ተደርጎ ሲታይም ኢ-ሞራላዊ ነው። እንደ ኒው ዮርክ ታይምስ ያሉ ግዙፍ የምዕራባውያን ሚዲያዎች ለወትሮው የአፍሪካን አዎንታዊ ዘገባዎች ሲሸፍኑ አይስተዋሉም ነበር።
በማሊ፣ ኒጀር እና በማዕከላዊ አፍሪካ አገራት የታየው የውጭ ጣልቃ ገብነትና ህዝባዊ ተቀውሞው አፍሪካውያን በምዕራባውያን የውጭ ፖሊሲ የተሰላቹ ስለመሆኑ ማሳያ ነው። እናም የምዕራባውያን የውጭ ፖሊሲ አውድ ዘመኑ ከሚጠይቀው የመከባበር እና ትብብርን መሰረት ያደረገ የግንኙነት ዓውድ መቃኘት እንዳለበት ሊረዱት ይገባል።
በምዕራብ አፍሪካ ህዝቦች የተንጸባረቁት የምዕራባውያን ጣልቃ ገብነት ጠል ሰልፎች እና ትናንት በኢትዮጵያ ህዝብ የታየው የ”ጣልቃ አትግቡብን” አቋም በምዕራባውያን የብዙሃን መገናኛዎች አዎንታዊ ሽፋን ማግኘት መቻሉ ዓለማዊ ለውጦችን ያገነዘበ ተደርጎ የሚወሰድ ነው።
የምዕራባውያን ፖለቲከኞችም ያረጀና ያፈጀ የ “እኛ እናውቅላቹሃለን” ዓይነቱ የፖሊሲ ትግበራ ከስሞ አዲስ የዓለም ሥርዓት ብቅ እየለ መሆኑን ተገንዝበው ግንኙነታቸውን በዚህ ልክ ሊያርሙትና ሊያስተካከሉት ይገባል።
በአፍሪካ ህዝቦች የሚደረጉት ጣልቃ ገብነት ጠል ሰልፎችን የዘመን ማብቂያ እና የአዲስ ዓለም ሥርዓት ብቅ ማለት ማሳያ ነውና።