"ኢትዮጵያውያን የግዛት አንድነታችንና የፖለቲካ ነፃነታችንን ለመወሰን መካሪ አንሻም"---የደብረ ብርሃን ከተማ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ - ኢዜአ አማርኛ
"ኢትዮጵያውያን የግዛት አንድነታችንና የፖለቲካ ነፃነታችንን ለመወሰን መካሪ አንሻም"---የደብረ ብርሃን ከተማ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ
ደብረ ብርሃን እና መተማ (ኢዜአ) ጥቅምት 13/2015---"ኢትዮጵያዊያን ሉዓላዊነታችንን፣ የግዛት አንድነታችንና የፖለቲካ ነጻነታችንን ለማስጠበቅ መካሪ የማንፈልግ ህዝቦች ነን" ሲሉ የደብረ ብርሃን ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ገለፁ።
"ለኢትዮጵያ እቆማለሁ፤ ድምፄን አሰማለሁ!'' በሚል መሪ ሀሳብ በደብረ ብርሃን እና በመተማ ከተሞች የተካሄዱ ህዝባዊ ሰልፎች ተጠናቀዋል።
የደብረ ብርሀን ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ካሳሁን እምቢአለ እንዳሉት የኢትዮጵያ ህዝብ አንዳንድ ምዕራባዊያን ሀገራት በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ እንዲገቡ አይፈቅድም።
"በኢትዮጵያ ላይ ያልተገባ ጫና የሚያደርጉ ሀገራት ኢትዮጵያ የምድረ ቀደምት የሰው ዘር መገኛ ከመሆኗ በላይ ለሰላም፣ ለነጻነትና ለህዝቦች እኩልነት ያላትን አቋም ከታሪካችን ቢማሩ ሀገር ለማፍረስ የሚጠነስሱትን ሴራ ያቆሙ ነበር" ብለዋል።
አንዳንድ ምዕራባውያን የሽብር ቡድኑን ከሞት ጉድጓድ አውጥተው ለማዳን እያደረጉት ያለው ግልፅ ጣልቃ ገብነትና ያልተገባ ጫና የኢትዮጵያ ህዝብ እንደማይቀበል ከዛሬው የህዝብ ተቃውሞ ድምጽ በላይ ማሳያ ሊኖር እንደማይችልም ተናግረዋል።
"ኢትዮጵያውያን ሉዓላዊነታችን፣ የግዛት አንድነታችንና የፖለቲካ ነፃነታችንን በራሳችን አቅም የምናስጠብቅ ህዝቦች መሆናችንን ዓለም ሊያውቅ ይገባል" ሲሉም ገልጸዋል።
"ሀገራዊ አንድነታችንን በማጠናከር የተደቀነብንን አደጋ ተባብረን በዘላቂነት እንቀለብሳለን'' ያሉት ደግሞ የምዕራብ ጎንደር ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ቢክስ ወርቄ ናቸው።
ተገቢ ያልሆነ ጣልቃ ገብነትና አሸባሪውን በተለያየ መንገድ የሚደግፉ አንዳንድ የምዕራባዊያን ሀገራትና ተቋሞቻቸው ትናትና ዛሬ ኢትዮጵያዊያን በነቂስ ወጥተው ያሰሙትን የተቋውሞ ድምጽ በማክበር ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ ጠይቀዋል።
ኢትዮጵያ ከራሷ አልፋ ለመላው አፍሪካ ሰላም መሆን የሰራችና በቀጣይም የምትሰራ የሰላም ተምሳሌት መሆኗን አስታውሰው፣ "በሉዓላዊነቷ ላይ ግን ህዝቦቿ እንደማይደራደሩ ሁሉም ሊያውቅ ይገባል" ብለዋል
ዋና አስተዳዳሪው እንዳሉት፣ የኢትዮጵያ ጠላቶች እስካሁን ባካሄዱት የሸፍጥ ሥራ አንድም ጊዜ ኢትዮጵያን ማሸነፍ ያልቻሉት በጀግኖች ልጆቿ አንድነትና አይደፈሬነት ነው።
በቀጣይም በህዝቦች መካከል ለዓመታት የቆየውን አንድነትና መደጋገፍ ይበልጥ በማጠናከር የጠላትን ቅስም መስበር እንደሚገባ አሳስበዋል።
"ያልተገባ ጫና የሚያደርጉና በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ በመግባት ግጭት እንዲባባስ እያደረጉ ያሉ አንዳንድ ምዕራባውያን የትግራይ ህዝብ በአሸባሪው ህወሓት የተደረገበት ጭቆና እንዲራዘም እያደረጉ መሆኑን ሊገነዘቡ ይገባል" ሲሉም ዋና አስተዳዳሪው ገልጸዋል።
"ቡድኑ ለህዝብ እንደማያስብ አንዱ ማሳያ ለትግራይ ህዝብ የገባን ሰብዓዊ እርዳታ ጭምር ለጦርነት ማዋሉ" ነው ያሉት ዋና አስተዳዳሪው፣ ህወሓት ከምስረታው ጀምሮ ለህዝብ ደንታ እንደሌለው በተግባር ሲያሳይ መቆየቱን ተናግረዋል፡፡
በገንዳ ውሃ ከተማ በተካሄደው ህዝባዊ ሰላማዊ ሰልፍ ላይ የተሳተፉት አቶ ቆያቸው አበራ በበኩላቸው እንዳሉት፣ "ለኢትዮጵያ የሚከፈልን ማንኛውም ዋጋ ከሀገር መከላከያ ሠራዊት ጎን በመሆን ለመክፈል ዝግጁ ነኝ" ብለዋል።
"ከመቼውም ጊዜ የበለጠ ህዝባዊ አንድነትን ማጠናከር፣ ለሠራዊቱ ደጀንነትን ማረጋገጥ እና ለሰላማችን ዘብ መቆም የጠላትን ሴራ የምንቀለብስበት መሳሪያችን ነው" ብለዋል።
በከተማው በተካሄደ ህዝባዊ ሰልፍ "በችግራችን ወቅት የነበራችሁ ሀገሮች ምስጋናችን ይድረሳችሁ! ፣ የትግራውያን ልማትና ብልፅግና የሚረጋገጠው ከእኛ ከወገኖቹ ጋር ነው! ፣ ሁለት ሠራዊት በአንድ ሉዓላዊ ሀገር አይኖርም! ፤ ሉዓላዊነታችንን አክብሩ! ፣ የኢትዮጵያ ህዝብ ዛሬም በሉዓላዊነቱ አይደራደርም! ፣ ለትግራይ ልማትና ሰላም ህወሓት ጋሬጣ ናት! ፣ በውክልና ጦርነት መጠቃት ይብቃ! የሚሉ መፈክሮች በሰልፈኞቹ ተስተጋብተዋል።
''ለኢትዮጵያ እቆማለሁ ድምፄን አሰማለሁ'' በሚል መሪ ቃል በከተሞቹ በተካሄደው ህዝባዊ ሰላማዊ ሰልፍ የሃይማኖት አባቶች፣ ተማሪዎች፣ የልዩ ልዩ አደረጃጀት ተወካዮች ፣ የህብረተሰብ ክፍሎች እንዲሁም የሲቪክ ማህበራት ተሳትፈዋል።