ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ህዝብ ከጥንት ጀምሮ በሃገሩ ጉዳይ የማይደራደር ነው ---በባህርዳር የሰልፍ ተሳታፊዎች

ባህር ዳር ጥቅምት 13/2014 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ህዝብ ከጥንት ጀምሮ በሃገሩ ጉዳይ የማይደራደር ነው ሲሉ የባህር ዳር ከተማ የሰልፍ ተሳታፊዎች ተናገሩ።

“ለኢትዮጵያ በነፃነት እቆማለሁ፤ ድምፄን በአደባባይ አሰማለሁ’’ በሚል መሪ ቃል የምዕራባዊያንን ጣልቃ ገብነትና አሸባሪውን ህወሃት የሚያወግዝ ህዝባዊ ሰልፍ ዛሬ በአማራ ክልል ባህር ዳርና በሌሎች የክልሉ ከተሞች ተካሂዷል።

ከሰልፉ ተሳታፊዎች መካከል አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡት እንዳሉት አንድን የሽብር ቡድን ደግፈው በሉዓላዊ አገር ጣልቃ የሚገቡ አካላት አደብ ሊገዙ ይገባል።

የቀድሞው ሰራዊት አባል ሻምበል በላይነህ  እንደገለጹት አንዳንድ ምእራባዊያን በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ በመግባት አሸባሪውን ህወሃት ወደፊት ለማምጣት አይን ያወጣ ድጋፍ እያደረጉ መሆኑን እያየን ነው።  

የሀገሪቱን ሉዓላዊነት በመዳፈር ተላላኪያቸውን ህወሃትን እየደገፉ ያለው የኢትዮጵያን አንጡራ ሃብት ለመዝረፍና ለመጠቀም ነው እንጂ ለአገራችን አስበው አይደለም ብለዋል።

የኢትዮጵያ ህዝብ ከጥንት ጀምሮ በሃገሩ ጉዳይ የማይደራደር ነው ያሉት ሻምበል በላይነህ፤ የአሁኑ ትውልድም የውጭ ጣልቃ ገብነትን በማውገዝ የሃገር አይደፈሬነትን እያሳየ ነው ብለዋል።

ሀገር ከሌለ ነግዶ ማትረፍም ሆነ ሰርቶ መግባት የለም ያሉት ደግሞ በሰላማዊ ሰልፉ የተሳተፉት የአማራ ክልል ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ከፍተኛ አመራር አቶ ክቡር ጌታቸው ናቸው።

ሰላም እንዳይኖርና ሀገሪቱን ለመበተን የሚሰሩ አንዳንድ የምዕራባውያን አገራት በውስጥ ጉዳያችን ጣልቃ ከመግባት ሊታቀቡ እንደሚገባም አመልክተዋል።

የንግዱ ማህበረሰብም ለመከላከያ ሰራዊቱና ለጸጥታ አካሉ የጀመረውን ድጋፍ በቀጣይም ሀገሪቱ ሰላም እስክትሆን ድረስ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል።

ሌላኛዋ የሰልፉ ተሳታፊ ወይዘሮ ሀናማርያም አማረ  በበኩላቸው በውስጥ ጉዳያችን ጣልቃ የሚገቡትንና የአሸባሪውን ህወሃት እንቅስቃሴ እናወግዛለን ብለዋል።

አንዳንድ የምዕራባዊያን ሀገራት ከኢትዮጵያ ላይ እጃቸውን እንዲያነሱና ኢትዮጵያ የቀደመ ሰላሟ እንዲመለስ ድጋፋቸውንና በሁሉም መስክ የድርሻቸውን እንደሚወጡም ተናግረዋል።

''የውጭ ጣልቃ ገብነት በኢኮኖሚም ሆነ በማንነታችን ላይ ሊያስከትል የሚችለውን ተፅዕኖ በመረዳት በጋራ ልንከላከል ይገባል'' ያለው ደግሞ ወጣት ጌትነት ምስጋናው ነው።

እንደ አንድ ኢትዮጵያዊ ጣልቃ ገብነትን ለማውገዝ በሰልፉ መሳተፉን ጠቅሶ፤ በሉዓላዊነታችን ላይ ጣልቃ እየገቡ ያሉት ሁሉ ቀጣይነት ባለው መንግድ ማውገዝ ይገባልም ብሏል።

አሁንም እንደ ቀደሙ አባቶቻችን በትግላችን ነጻነታችንንና አልደፈር ባይነታችንን ለማስከበር ከምንጊዜውም በላይ ቆርጠን ተነስተናል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም