በግብርናው መስክ የተጀመሩ የልማት ስራዎች በምግብ ራስን ከመቻል ባሻገር ለኢኮኖሚ ሉዓላዊነት መሰረት የሚጥሉ ናቸው- የመንግስት የስራ ሃላፊዎች - ኢዜአ አማርኛ
በግብርናው መስክ የተጀመሩ የልማት ስራዎች በምግብ ራስን ከመቻል ባሻገር ለኢኮኖሚ ሉዓላዊነት መሰረት የሚጥሉ ናቸው- የመንግስት የስራ ሃላፊዎች
ጥቅምት 13/2014/ኢዜአ/ በግብርናው መስክ ምርታማነትን ለማሳደግ እየተከናወኑ ያሉ ስራዎች በምግብ ራስን ከመቻል ባሻገር ለኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ሉዓላዊነት መሰረት የሚጥሉ መሆናቸውን ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች ተናገሩ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አቢይ አህመድን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች በጅማ ዞን እየተከናወኑ ያሉ የተለያዩ የልማት ስራዎችንና የቦንጋ ዩኒቨርሲቲን የልማት እንቅስቃሴ ጎብኝተዋል፡፡
በጉብኝቱ ላይ የተሳተፉ ሚኒስትሮች በአካባቢው እየተከናወኑ ያሉ የግብርና ልማት ስራዎች እንደ አገር ትልቅ የሽግግር አቅም መሆናቸውን ገልጸዋል።
በአካባቢው በአትክልትና ፍራፍሬ፣ በሰብል ልማትና ሌሎችም መስኮች የሚያተኩሩ ተግባራት በመከናወን ላይ በመሆናቸው አድንቀዋል።
በግብርናው መስክ ምርታማነትን ለማስፋት እየተከናወኑ ያሉ ስራዎች በምግብ ራስን ከመቻል ባሻገር ለኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ሉዓላዊነት መሰረት የሚጥሉ መሆናቸውን ገልጸዋል።
የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ገብረመስቀል ጫላ፤ በተለያዩ አካባቢዎች የግብርና እና ሌሎችም የልማት ስራዎች በምግብ ራስን ለመቻል ለሚደረገው ጥረት የስኬት መንገድ ማሳያዎች መሆናቸውን ተናግረዋል።
በከተሞች ጭምር የግብርና ልማት በስፋት በመከናወን ላይ መሆኑን ጠቅሰው በብዙ መልኩ የተሳኩ ውጤቶች እየተመዘገቡ መሆኑን ገልጸዋል።
የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ፤ በቦንጋ የታየው አስደናቂ ስራ በሌሎችም ተመሳሳይ የልማት ስራ ከተከናወነ የኢትዮጵያ ሁለንተናዊ ስኬት የሚረጋገጥ መሆኑን ያመላከተ ነው ብለዋል።
በተለያዩ አካባቢዎች እንደ አገር የሚታዩት የግብርና ልማት ስራዎችም አስደናቂ መሆናቸውን ተናግረዋል።
በሚኒስትር ማዕረግ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ተጠሪ አቶ ተስፋዬ ቤልጅጌ፤ በበኩላቸው በጉብኝታችን በአካባቢው ቀደም ሲል ያልተለመዱ አዳዲስ የግብርና ልማት ስራዎችን በስፋት ተመልክተናል ብለዋል።
በዚህም የኢትዮጵያን በምግብ ራስን የመቻል እንዲሁም የእድገትና ብልጽግና ተስፋ እውን የማድረግ ትክክለኛ አቅጣጫ መሆኑ የታየበት እንደሆነ ገልጸዋል።
በብልጽግና ፓርቲ የምርጫ ጉዳይ ሃላፊ ዛዲግ አብርሃ፤ በሁሉም መስክ የተመለከትናቸው የልማት እንቅስቃሴዎች ኢትዮጵያ ከዝቅተኛ አምራችነት በመሸጋገር ላይ መሆኗን የሚያመላክቱ ናቸው ብለዋል።
እንደ አገር በማክሮ ኢኮኖሚ እና በግብርና ልማት ለውጥና እመርታዎች እየታዩ መሆኑንም ገልጸዋል።