ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ከመደበኛ ተግባራቸው ባለፈ የግብርና ልማት አጋዥ ሊሆኑ ይገባል- ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን - ኢዜአ አማርኛ
ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ከመደበኛ ተግባራቸው ባለፈ የግብርና ልማት አጋዥ ሊሆኑ ይገባል- ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን
ጥቅምት 13/2015/ኢዜአ/ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ከመደበኛ ተግባራቸው ባለፈ በዘመናዊ አሰራር በማገዝ ለኢኮኖሚ ልማት የላቀ ሚና ሊኖራቸው እንደሚገባ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ተናገሩ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አቢይ አህመድን ጨምሮ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንንና ሌሎች ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች በጅማ ዞን እየተከናወኑ ያሉ የልማት ስራዎችንና የቦንጋ ዩኒቨርሲቲን የልማት እንቅስቃሴ ጎብኝተዋል፡፡
ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች ከጎበኟቸው ስፍራዎች መካከል በቦንጋ ዩኒቨርሲቲ እየተከናወነ ያለው የግብርና ልማት ስራ አንዱ ነው።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን፤ ዩኒቨርሲቲው መደበኛ የመማር መስተማርና የምርምር ስራዎችን ከአካባቢ ጥበቃ ጋር አጣምሮ እያከናወነ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
ዩኒቨርሲቲው የወተት ልማትን ጨምሮ በግብርናው መስክ አርአያነት ያለው ተግባር እያከናወነ መሆኑን ጠቅሰው ሌሎች ከፍተኛ የትምህርት ተቋማትም ይህንኑ ፈለግ ሊከተሉ ይገባል ብለዋል።
ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ከሰው ኃይል ልማት ባሻገር የአገር ኢኮኖሚን በሚደግፉ ስራዎች በመሰማራት ለሁሉን አቀፍ ልማት የሚጠበቅባቸውን ድጋፍ ሊያደርጉ እንደሚገባ አንስተዋል።
ሌላኛው በከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች ከተጎበኙ ስፍራዎች መካከል በጅማ ዞን እየተከናወነ ያለው የሩዝ ምርት ተጠቃሽ ነው።
ከዚህ ቀደም በአከባቢው የሩዝ ምርት ልማት የተለመደ እንዳልነበር ያስታወሱት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ የአከባቢው አርሶ አደሮች የሩዝ ምርት ልማትን በመጀመር ውጤታማ ስራ ማከናወናቸውን ተናግረዋል
አርሶ አደሮቹ በአከባቢው ያለውን ጸጋ በመጠቀም በዓመት ሁለት ጊዜና ከዚያ በላይ ሊያመርቱ እንደሚገባም ነው የተናገሩት
በዞኑ እየተከናወነ ያለው የግብርና ልማት ስራ ራስን ከመቻል ባለፈ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ በመደገፍ ረገድ ትልቅ ተስፋ የሚሰጥ መሆኑንም ተናግረዋል።
በየደረጃው ያሉት አመራሮች ለዘርፉ ውጤታማነት ላበረከቱት አስተዋጽኦ ምስጋና አቅርበው፣ ለአርሶ አደሩ የሚያደርጉትን ድጋፍ አጠናክረው እንዲቀጥሉ አሳስበዋል።