የአንዳንድ ምዕራባውያንን ያልተገባ ጫና እና አሸባሪውን ህወሓት የሚያወግዙ ሰልፎች በጎንደር፣ እንጅባራ እና ወልዲያ ከተሞች እየተካሄዱ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የአንዳንድ ምዕራባውያንን ያልተገባ ጫና እና አሸባሪውን ህወሓት የሚያወግዙ ሰልፎች በጎንደር፣ እንጅባራ እና ወልዲያ ከተሞች እየተካሄዱ ነው
ጎንደር፣ እንጅባራ እና ወልዲያ (ኢዜአ) ጥቅምት 13/2015----በጎንደር፣ እንጅባራና ወልዲያ ከተሞች አንዳንድ ምዕራባውያን በኢትዮጵያ ላይ እያደረጉት ያለውን መርህ አልባ ጫና እና አሸባሪውን ህወሓት የሚቃወሙ ህዝባዊ ሰልፎች እየተካሄዱ ነው።
በጎንደር ከተማ የምዕራባውያንን ጣልቃ ገብነትና ያልተገባ ጫና ለማውገዝ እየተካሄደ ባለ ህዝባዊ ሰልፍ በከተማዋ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች እየተሳተፉ ነው።
የከተማውና የአካባቢው ነዋሪዎች "ለኢትዮጵያ እቆማለሁ፤ ድምጼንም አሰማለሁ!’’ በሚል መሪ ቃል ከማለደው ጀምሮ በከተማው መስቀል አደባባይ ድምጻቸውን እያሰሙ ነው።
በሰልፉ ላይ ነዋሪቹ ይዘዋቸው ከወጡ መፈክሮች መካከል "በሰብአዊ እርዳታ ስም የውጭ ጣልቃ ገብነት ይቁም! ፤ በውክልና ጦርነት መጠቃት ይብቃ! ፤ በድርድር ስም ሰቆቃችንና የህወሓት እድልን ማራዘም ይብቃ! " የሚሉ ይገኙባቸዋል።
ከእዚህ በተጨማሪም ለዘላቂ ሰላም ህወሓት ትጥቅ ይፍታ! ፣ በሉአላዊነታችን አንደራደርም!፤ የትግራይ ህዝብ ወገናችን ነው! ጁንታው ጠላታችን ነው! የሚሉ መፈክሮችን በሰልፈኞቹ በመስተጋባት ላይ ናቸው።
በህዝባዊ ሰልፉ ወጣቶች፣ ሴቶች፣ የመንግስት ሰራተኞች፣ ተማሪዎች፣ነጋዴዎች፣ የሀገር ሽማግሌዎችና ጀግኖች አርበኞች እየተሳተፉ ነው።
በተመሳሳይ በአዊ ብሔረሰብ አስተዳደር እንጅባራ ከተማ የውጭ ጣልቃ ገብነትን እና ሽብርተኛውን ህወሓት የሚያወግዝ ህዝባዊ ሠልፍ በመካሄድ ላይ ነው።
ሰልፈኞቹ አሸባሪውን ህወሓት በማውገዝ አንዳንድ ምዕራባውያንን በሉዓላዊነትና በኢትዮጵያ ክብር ላይ ጣልቃ እየገቡ ያልተገባ ጫና ለመፍጠር የሚያደርጉትን እንቅስቃሴ እንዲያቆሙ ጠይቀዋል።
በሕዝባዊ ሠልፉ ላይ የሀገር ሽማግሌዎች፣ ወጣቶችና የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች እየተሳተፉ ሲሆን የአገው ፈረሰኞች ለሰልፉ ድምቀት ሆነዋል።
የከተማዋ ነዋሪዎች “በውክልና ጦርነት መጠቃት ይብቃ!፣ በሰብዓዊ ዕርዳታ ስም ጣልቃ ገብነቱ ይቁም!፣ ህወሓት የችግራችን ሁሉ ምንጭ ነው!፣ የትግራይ ህዝብ ወዳጅ፤ ህወሓት ጠላታችን ነው!፣ በድርድር ስም የአሸባሪውን ዕድሜ ማራዘም ይብቃ!" የሚሉና መሰል መፈክሮች በማሰማት ላይ ናቸው።
በተመሳሳይ የአሸባሪውን ህወሓት ቡድን ጥፋት የሚያወግዝ፣ የውጭ ያልተገባ ጣልቃ ገብነት የሚቃወምና ለመከላከያ ሠራዊት ድጋፍ የሚገለጽበት ህዝባዊ ሰላማዊ ሰልፍ በወልዲያ ከተማ እየተካሄደ ነው።
”ለኢትዮጵያ እቆማለሁ፤ ድምፄን አሰማለሁ!” በሚል መሪ ሀሳብ እየተካሄደ ባለው ህዝባዊ ሰልፍ ከከተማውና አጎራባች ቀበሌ ነዋሪዎች ህዝቡ በነቂስ ወጥቶ ድምፁን እያሰማ ይገኛል።
የሰልፉ ተሳታፊዎች “የምዕራባውያን ሀገራት ያልተገባ ጫናን እቃወማለሁ! ፣ በሰብዓዊ እርዳታ ስም ጣልቃ ገብነት ይቁም!፣ የትግራይ ህዝብ ወገናችን ነው!፣ ህወሓት ጠላታችን ነው! ፣ ህወሓት አሸባሪ ፓርቲ እንጂ ሃገር አይደለም! ” የሚሉ መፈክሮችን አሰምተዋል።
በተጨማሪም አሸባሪው ህወሓት በ27 ዓመታት አገዛዙ ባንገሸገሻቸው የኢትዮጵያ ህዝቦች ከስልጣኑ የተወገደ ድርጅት መሆኑን ሰልፈኞቹ ገልጸዋል።
ህወሓት በስልጣን ዘመኑም ሆነ ዛሬም ኢትዮጵያን ለማፈራረስ ከውጭ ደጋፊዎቹ ጋር ተግቶ እየሰራ መሆኑን ጠቅሰዋል።
በተለይ ለ3ኛ ጊዜ ጦርነት በመክፈት ምንም ለሰላም ቦታ እንደሌለው በግላጭ ማሳየቱን ሰልፈኞቹ ተናግረዋል።
ይህን አሸባሪ ቡድን በመደገፍ አንዳንድ የምዕራባውያን ሀገራት በኢትዮጵያ ላይ ያልተገባና መርህ አልባ ጫና በማድረግ ቡድኑን ከሞት አፋፍ ለመታደግ የሚያደርጉትን ጥረት እንደሚቃወሙ ሰልፈኞቹ ገልጸዋል።
ሠልፈኞቹ ይህንን የምዕራባውያንን የጣልቃ ገብነት ድርጊት አውግዘው፤ መንግስት የሀገር ሉአላዊነትንና ሰላምን ለማረጋገጥ የሚያደረገውን ጥረት ሙሉ በሙሉ እንደሚደግፉ አረጋግጠዋል።
ሰልፈኞቹ በመልዕክታቸው የትግራይ ወገኖቻችንም ከአሸባሪው አፈና ለመላቀቅ እንዲችሉና ለዚህም ስኬት የድርሻቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።
ለጀግናው የሀገር መከላከያ ሠራዊት በተለያየ መንገድ የጀመሩትን ድጋፍ አጠናክረው እንደሚቀጥሉም ሰልፈኞቹ በአንድ ድምጽ አረጋግጠዋል።