ቀጥታ፡

በደብረብርሃንና በገንዳውሃ ከተሞች የምእራባዊያንን ጣልቃ ገብነትና አሸባሪውን ህወሓት የሚያወግዙ ሰልፎች እየተካሄዱ ነው

ጥቅምት 13/2015 (ኢዜአ) በምዕራብ ጎንደር ዞን የገንዳውሃ ሕዝባዊ ሰለፍ ተሳታፊዎች አሸባሪው ህወሓት ትግራይን ጨምሮ በመላ ኢትዮጵያ በፈጸመው ኢ-ሰብዓዊ ድርጊቶችና ባደረሰው ጥፋት ተጠያቂ መሆኑን ገልጸዋል።

ሰልፈኞቹ አንዳንድ ምዕራባውያን የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ሊያከብሩ ይገባል፤ በገፉን ቁጥር ቀጥ ብለን እንቆማለን እንጅ አንወድቅም፤ ጠላቶቻችን ኢትዮጵያዊ መሆናችንን ሊዘነጉት አይገባም የሚሉ መልዕክቶችን እያሰሙ ነው።

የኢትዮጵያ ህዝብ ዛሬም በሉዓላዊነቱ አይደራደር፤በውክልና ጦርነት መጠቃት ይብቃ፤ ለትግራይ ልማትና ሰላም ህወሓት ጋሬጣ ነው፤ የትግራይ ልማትና ብልፅግና የሚረጋገጠው ከእኛ ከወገኖቹ ጋር ነው፤ ሁለት ሰራዊት በአንድ ሉዓላዊ ሀገር አይኖርም፤ ህወሓት የሰላም ፀር ነው የሚሉ መልእክቶች በሰልፈኞቹ ተስተጋብተዋል።

በችግራችን ወቅት ከጎናችን ለቆማችሁ የኢትዮጵያ ወዳጅ ሀገሮችና ሕዝቦች ምስጋናችን ይድረሳችሁ የሚል መልዕክትም አያስተላልፈዋል፡፡

በተመሳሳይ "ለኢትዮጵያ እቆማለሁ ድምፄን አሰማለሁ በሚል መሪ ቃል የአሸባሪውን ህወሓትና ተላላኪዎቹን የሚያወግዝ ህዝባዊ ሰልፍ በደብረ ብርሀን ከተማ እየተካሄደ ነው።

ከሰልፉ ተሳታፊዎች መካከል የቀድሞ ወታደርና አካል ጉዳተኛ ሞላ ድንበሩ አሸባሪው ህወሓት የሰላም ጸርነትና አንዳንድ ምዕራባዊያን በኢትዮጵያ ላይ እያደረሱ ያለውን ያልተገባ ጣልቃ ገብነት እንዲያቆሙ ለመጠየቅ ሰልፍ መውጣቱን ተናግሯል።

አቶ ደሱ ምትኩ የሀገር ሉዓላዊነትን ለማስከበር ዋጋ እየከፈለ ለሚገኘው ለጀግናው የሀገር መከላከያ ሰራዊት ድጋፋቸውን ለመግለጽና በኢትዮጵያ ላይ ያልተገባ ጫና እየፈጠሩ ያሉ አካላትን ለመቃወም ስልፍ ወጥቻለሁ ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም