ኢትዮጵያ በደምና በአጥንት የተገነባች ታላቅ ሀገር በመሆኗ ታፍራና ተከብራ ለዘላለም ትኖራለች-ጥንታዊ ጀግኖ አርበኞች - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ በደምና በአጥንት የተገነባች ታላቅ ሀገር በመሆኗ ታፍራና ተከብራ ለዘላለም ትኖራለች-ጥንታዊ ጀግኖ አርበኞች
አርባ ምንጭ ጥቅምት 12/2015 (ኢዜአ) ኢትዮጵያ በደምና በአጥንት የተገነባች ታላቅ ሀገር በመሆኗ በጀግኖች ልጆቿ ታፍራና ተከብራ ለዘላለም ትኖራለች ስሉ የጋሞ እና ጎፋ ዞኖች ጥንታዊ የኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማህበር አመራርና አባላት አስታወቁ፡፡
ወጣቱ ትውልድ አባቶቹ ያቆዩትን ሀገር ሉዓላዊነቷንና ክብሯን ጠብቆ ለመጪው ትውልድ የማስተላለፍ አደራ እንዳለበትም አስገንዝቧል፡፡
የጋሞ እና ጎፋ ዞኖች ጥንታዊ ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማህበር ሊቀመንበር አቶ ተስፋዬ ገመዳ ለኢዜአ እንደገለጹት ኢትዮጵያ በታሪኳ ብዙ ፈተናዎች ቢገጥሟትም እስካሁን ፀንታ የቆየችው አባቶች በከፈሉት የደምና የአጥንት ዋጋ ነው፡፡
በሀገራችን ብዝሃነነት ተምሳሌት ሀገር ብትሆንም ልጆቿ በሀገር ጉዳይ አንድ በመሆናችን ነፃነቷን ጠብቃ ጸንታ መኖሯን ገልጸዋል፡፡
በጀግኖች ልጆቿ አጥንትና ደም የተገነባችውን ሀገር አሸባሪው ህወሓት ላለፉት ሶስት አስርታት ያህል መንግሥት ሆኖ ሲመራት ሀብቷን ሲቀራመት መቆየቱን አስታውሰዋል፡፡
አንዳንድ ምዕራባዊያን በተለያየ ስልት የሀገራችን ሉዓላዊነት ለመዳፈር የሚሹት ነፃነቷን ጠብቃ የኖረች ሀገር በመሆኗ ነው ብለዋል
በመሆኑም ወጣቱ ትውልድ እንደ አባቶች ሁሉ አንድነቱን በማጠናከር የውስጥና የውጭ ጠላቶቻችን በማሳፈር ለመጭው ትውልድ ጠንካራዋን ኢትዮጵያን ከነክብሯ የማስረከብ አደራ እንዳለበትም አስገንዘበዋል፡፡
ኢትዮጵያ በጀግኖች ልጆቿ ከ3 ሺህ ዓመታት በላይ ነፃነቷን ጠብቃ የኖረች ሀገር መሆኗን የተናገሩት ደግሞ አርበኛው ሻምቤል ሀብተገብርኤል ጫቦ ናቸው፡፡
የኢትዮጵያ ህዝብ ከነኩት የማይለቅና ከሰላም ወዳድ ሀገሮች ጋር ደግሞ ተባብሮ የሚኖር ኩሩ ህዝብ ነው ሲሉ ገልጸዋል፡፡
ኢትዮጵያን በቅኝ ለመግዛት ሞክረው ያልተሳካላቸው አካላት በአሸባሪው ህወሓት ሴራ እየሸረቡ መሆናቸውን ጠቅሰው፤ በዚህ የፈተና ወቅት ከሀገራችን ጎን በመሆን የተባበሩ ሀገሮች ምስጋና ይገባቸዋል ብለዋል፡፡
ሌላኛው የማህበሩ አባል የአስር አለቃ ተስፋዬ ገብረአብ በበኩላቸው ኢትዮጵያ ጸንታ የኖረችው በህዝቦቿ አንድነት መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት በሚዳፈር መልኩ በውስጥ ጉዳይዋ ለመግባት ከታች ላይ እየባዘኑ ያሉ አንዳንድ ምዕራባዊያን እጃቸውን ከኢትዮጵያ ላይ እንዲያነሱ ጠይቀዋል፡፡
አሸባሪው ህወሓት ሀገር ለማፍረስ የከፈተውን ጦርነት መንግሥት በብቃት እየተመከተ መሆኑን ገልጸው የትግራይ ክልል ህዝብም ከመንግሥት ጎን ሆኖ የሽበር ቡድኑን በቃህ ሊለው ይገባል ብለዋል፡፡