ቀጥታ፡

በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ የሚገቡ አንዳንድ ምዕራባዊያን ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጠየቁ

አርባ ምንጭ፤ ጥቅምት 12/2015 (ኢዜአ)፡- አሸባሪው ህወሃትን በመደገፍ በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ የሚገቡ አንዳንድ ምዕራባዊያን ሃገራት ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጠየቁ።

በሀገሪቱ ጠላቂ ሰላም ለማምጣት መንግስት የሄደበት ርቀት ተገቢ መሆኑንና እንደሚደግፉትም አስታውቀዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዴሞክራትክ ህብረት/ኢዴህ/ የደቡብ ክልል ሰብሳቢ አቶ ሃይለጊዮርጊስ አዴሎ፤ ሀገሪቱን መጠበቅና ማልማት ሁሉም የዜግነት ግዴታ እንዳለበት ለኢዜአ ተናግረዋል፡፡

ሆኖም አሸባሪው  ህወሃት “እኔ ካልገዛኋት ስኦልም ቢሆን ገብቼ አፈርሳታለሁ” በማለት በግልጽ ኢትዮጵያን ለማፍረስ የተነሳ  ቡድን መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ይህ የእናት ጡት ነካሽ  ቡድን በስልጣን ላይ በነበረባቸው ጊዜያት እንደፈለገው በመሆን ዜጎችን ለሞትና ስቃይ ሲዳርግ መቆየቱን አውስተው፤  በህዝብ ትግል  ተገፍቶ ስልጣኑን ካጣ በኋላ ከአመሰራረቱ ጀምሮ የነበረውን የሽፍታነት ባህሪውን በግልጽ እያሳየ እንደሚገኝ አመላክተዋል።

በመንግስት የቀረበለትን  የሰላም አማራጮችን በመርገጥ በህዝብ ላይ ተደጋጋሚ ጦርነት መክፈቱ የአደባባይ ሚስጢር መሆኑን ጠቅሰዋል።

የጦርነቱ ጠንሳሹ አሸባሪው ህወሃት በህዝቡ ላይ ግድያና ውድመት ሲፈጽም ዝም በማለት መንግስት የተጣለበትን ሀገራዊና ህዝባዊ አደራ ለመወጣት ሲንቀሰቀስ ደግሞ ቡድኑን ወግነው ጩኸት የሚያሰሙ አንዳንድ ምዕራባዊያን የተባበሩት መንግስታት  ድርጅትን መርሆን እየጣሱ ናቸው ብለዋል፡፡

ቡድኑ ከኢትዮጵያ ታሪካዊ  ጠላቶች ጋር ጭምር በማበር ሀገር የማፍረስ ግቡን ለማሳካት እየጣረ እንደሚገኝ ገልጸው፤  ከዚህ ቡድን ጀርባ ያሉ አካላት ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ ጠይቀዋል፡፡

መንግስት የሀገሪቱን ሰላምና አንድነት ለማረጋገጥ ችግሮችን በውይይት ለመፍታት ከመሻትም በላይ የተናጥል ተኩስ አቁም እርምጃ እስከ መውሰድ ሃላፊነቱን መወጣቱን አውስተዋል።

ሰላም ለማስፈን መንግስት  የሄደበት ርቀት ያደነቁት አቶ ሃይለጊዮርጊስ ፤ ለኢትዮጵያ ሉዓላዊነትና ክብር መጠበቅ ፓርቲያቸው ከመንግስት ጎን እንደሚቆም አስታውቀዋል፡፡

የኢትዮጵያ ሶሻል ዴሞክራቲክ ፓርቲ/ኢሶዴፓ/ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል አቶ ዳጉ ዶባሞ በበኩላቸው፤ አሸባሪው ህወሃት በሀገራችን ላይ ለዘመናት እያስከተለ ያለው ኪሳራ አፍሪካን ለመቀራመት የተጠናወቱ የቅኝ ገዢዎች ተልዕኮ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የአንዳንድ የምዕራባዊያን ቅኝ ገዢ ጉዳይ አስፈጻሚ ፈረስ ፤ እነሱ  ደግሞ ጋላቢዎች መሆናቸውን አመላክተው፤ ይህ አሮጌ አስተሳሰብ ደግሞ በዚሁ በ21ኛው ክፍለ ዘመን በሉዓላዊት ሀገር ላይ የማይቻል ነው ያሉት፡፡

ኢትዮጵያዊያን  ለሀገራቸው ሉዓላዊነትና ለነፃነታቸው የማይደራደሩ መሆኑን መገንዘብ እንደሚገባ ያመለከቱት አቶ ዳጉ ፤ አሸባሪውን ህወሃት በማገዝ በሀገሪቱ የሚደረግ የውጭ ጣልቃገብነት ታሪካችንና ስነ-ልቦናችን ከመዘንጋት የመጣ ነው ብለዋል፡፡

በሀገር ላይ ተደጋጋሚ ጦርነት በመክፈት ሰብአዊና ቁሳዊ ኪሳራ እያደረሰ ያለውን የአሸባሪውን ተግባር መደገፍ ተገቢ አለመሆኑን በመግለጽ ለቡድኑ  ባልተገባ መንገድ ጥብቅና የቆሙ አንዳንድ ምዕራባዊያን  ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ ጠይቀዋል።

ሀገሪቱንና ህዝቦቿን ለመጉዳት አየጣሩ ያለው አሸባሪው ህወሃትና ተላላኪው ሽኔ በህግ አግባብ ሊጠየቁ እንደሚገባ ያመለከቱት ደግሞ  የዶንጋ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት ፕሬዚዳንት አቶ አየለ መካንጎ ናቸው፡፡

አሸባሪውን በመደገፍ በሀገራችን ላይ ጫና ለመፍጠር የሚሞክሩ አካላት ተቀባይነት እንደሌለው ተረድተው ከድርጊታቸው እንዲቀጠቡ ጠይቀዋል፡፡

በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም ለማምጣት መንግስት አማራጮችን በማመቻቸት  የሄደበት ርቀት ተገቢ መሆኑንና  እንደሚደግፉትም አስታወቀዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም