አንዳንድ ምዕራባውያን አገራት አሸባሪው ሕወሓትን ለማትረፍ እየሰሩ ነው - አቶ ኡሞድ ኡጁሉ - ኢዜአ አማርኛ
አንዳንድ ምዕራባውያን አገራት አሸባሪው ሕወሓትን ለማትረፍ እየሰሩ ነው - አቶ ኡሞድ ኡጁሉ
ጋምቤላ (ኢዜአ) ጥቅምት 12/2015(ኢዜአ) "አንዳንድ ምዕራባውያን አገራት መንግስት የአገርን ሉዓላዊነት ለማስከበር ከሚወስደው እርምጃ በተቃርኖ በመቆም አሸባሪው ሕወሓትን ለማትረፍ እየሰሩ ነው" ሲሉ የጋምቤላ ክልል ርዕስ መስተዳድር አቶ ኡሞድ ኡጁሉ ገለጹ።
አገራቱ የሽብር ቡድኑን በመጠቀም በኢትዮጵያ ላይ የውክልና ጦርነት እያካሄዱ ይገኛል ብለዋል።
‘‘ለኢትዮጵያ እቆማለሁ፤ ድምጼን አሰማለሁ!’’ በሚል መሪ ሃሳብ አሸባሪውን ህወሓትንና የምዕራባውያን ያልተገባ ጣልቃ ገብነት የሚያወግዝ ሰልፍ ዛሬ በጋምቤላ ከተማና አካባቢው ተካሄዷል።
የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኡሞድ ኡጁሉ አንዳንድ ምዕራባውያን አገራት የአፍሪካ የነጻነት ተምሳሌት በሆነችው ኢትዮጵያ ላይ በሕወሓት የሽብር ቡድን አማካኝነት የውክልና ጦርነት እያካሄዱነው ብለዋል።
መንግስት የአገርን ሉዓላዊነትና የዜጎችን ደህንነት ለመጠበቅ የሚያደርገውን ጥረት ወደ ጎን በመተው የሽብር ቡድኑ እኩይ ትግባር በመሸፈን ሊያተርፉት እየሞከሩ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
በመገናኛ ብዙሃኖቻቸው አማካኝነት የሽብር ቡድኑን ሀሰተኛ መረጃ ተቀብለው በማሰራጨት እውነትን ለመደበቅ የሚያደርጉት ጥረት የምዕራባውያኑ አድሏዊነት ሌላኛው መገለጫ መሆኑን ተናግረዋል።
የሽብር ቡድኑ ከውጪ ታሪካዊ ጠላቶች ጋር በመሆን የከፈተውን ዘመቻ በመቀልበስ ሉዓላዊነትንና የግዛት አንድነትን ለማስጠበቅ በወገን ጦር እየተደረገ ላለው ተጋድሎ የክልሉ ሕዝብና መንግስት ደጀንነቱን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ነው ርዕሰ መስተዳድሩ ያመለከቱት።
የሰልፉ ታዳሚዎች በበኩላቸው በግንባር እየተዋደቀ ላለው የወገን ጦር ሕዝባዊ ደጀንነትን መግለጽ እንደሚያስፈልግ ጠቁመው፣ ለአገር ሉዓላዊነትና ክብር ሲሉ ማንኛውንም መስዋዕትነት ለመክፈል ዝግጁ ነን ብለዋል።
"አንዳንድ ምዕራባውያን አገራት በውክልና ጦርነት ኢትዮጵያን ለማፍረስ የሚያደርጉትን ሴራ ሊያቆሙ ይገባል" ሲሉ ገልጸዋል።
የሽብር ቡድኑና ሌሎች የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች በአገር ሉዓላዊነት ላይ የሚቃጡትን ትንኮሳዎች በጋራ እንመክታለን ነው ያሉት የሰልፉ ተሳታፊዎች።
በጋምቤላ ከተማና አካባቢው በተካሄደው ሰልፍ በሺዎች የሚቆጠሩ የከተማ ነዋሪዎችና ሌሎች የሕብረተሰብ ክፍሎች ተሳትፈዋል።