አንድነታችንን አጠናክረን ለሠራዊታችን የምንሰጠው ድጋፍ እንቀጥላለን - የአሶሳ ነዋሪዎች - ኢዜአ አማርኛ
አንድነታችንን አጠናክረን ለሠራዊታችን የምንሰጠው ድጋፍ እንቀጥላለን - የአሶሳ ነዋሪዎች
አሶሳ፤ ጥቅምት 12 ቀን 2015 (ኢዜአ) ፡- አንድነታችንን ከምንጊዜውም በላይ በማጠናከር ለሠራዊታችን የምንስጠውን ድጋፍ እንቀጥላለን ሲሉ በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል የአሶሳ ከተማ ነዋሪዎች አስታወቁ።
የውጪ ጣልቃ ገብነት በመቃወና የሃገር መከላከያ ሠራዊትን በመደገፍ ዛሬ በአሶሳ ከተማ በተካሄደው ህዝባዊ ሰልፍ ከተሳተፉ ነዋሪዎች ወይዘሮ ሰናይት ቀነአ፤ ማንም ኢትዮጵያን እንዲነካ ስለማልፈልግ በሰላማዊ ሰልፉ ተሳትፊያለሁ ብለዋል፡፡
ለየትኛውም የውጭ ሃይል ተጽእኖ ኢትዮጵያ ተንበርክካ ባለማወቋ ፤ ሽብርተኛው ህወሃት በከፈተው ጦርነት በቅርቡ ግብዓተ መሬቱ እንደሚፈጸም አምናለሁ ብለዋል፡፡
አሸባሪው ህወሃት በሃገር መከላከያ ሠራዊት ላይ የፈጸመውን ታሪክ የማይረሳው ጥቃት በማስታወስ አስተያየታቸውን የጀመሩት ደግሞ አቶ አህመድ የኑስ ናቸው፡፡
የሽብር ቡድኑ መንግስት ያቀረበለትን የሠላም አማራጭ በመርገጥ ንጹሃን ኢትዮጵያውያንን ማስጨረሱን መቀጠሉን ጠቅሰዋል፡፡
አንድነታችንን ከምንጊዜውም በላይ በማጠናከር ሠራዊታችንን መደገፋችን ተጠናክሮ የሚቀጥል ጉዳይ ነው ሲሉም ነዋሪው አክለዋል፡፡
አቶ ሻምበል አንበሳ በበኩላቸው፤ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ ለማዳከምና የህዝቦችን አንድነት ለማጥፋት የውስጥ እና የውጭ ጠላቶቻችን ተቀናጅተው እየሠሩ ነው ብለዋል።
ዓላማቸው ደግሞ ህወሃትን ወደ ስልጣን በማምጣት የ27 ዓመቱን የግፍ አገዛዝ መመለስ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
መፍትሔው ኢትዮጵያዊ አንድነታችንን በማጠናከር የአባቶቻችንን ታሪክ መድገምና ሠላማችንን በማስጠበቅ ልማታችንን ማስቀጠል ነው ሲሉ ገልጸዋል፡፡
የአሶሳ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ አብዱልሙኒየም አብዱልዋሂድ፤ የከተማዋ ነዋሪዎች በነቂስ ወጥተው ያደረጉት ሰልፍ ለሀገራቸው ያላቸውን ፍቅርና ክብር ያሳየ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ይህም ኢትዮጵያን ለማፍረስ ለሚጥሩ የውስጥ ባንዳዎችም ሆነ የውጪ ታሪካዊ ጠላቶች በግልጽ መልስ የሰጠ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሃሰን ባደረጉት ንግግር፤ ኢትዮጵያ በየጊዜው የገጠማትን ወራሪ በመመከት በተለይም ለጥቁር ህዝቦች ተጋድሎ ፈር ቀዳጅ እንደሆነች አውስተዋል፡፡
በአንጻሩ በእርስ በእርስ ግጭት እንዲሁም በሰው ሰራሽ እና የተፈጥሮ ችግሮች ሳቢያ የተፈጥሮ ሃብታችንን በአግባቡ ሳናለማ ለረሃብ ተጋልጠን ቆይተናል ብለዋል፡፡
ይህም እርዳታ ጠባቂ አድርጎናል ነው ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፡፡
ይህ ታሪክ እየተቀየረ መምጣቱን የገለጹት አቶ አሻድሊ፤ ስንዴ በማምረት ወደ ውጭ ለመላክ የተደረገው የሚገኘው ዝግጅት በማሳያነት ጠቅሰዋል፡፡
በእርዳታ ሽፋን እጃችንን ለመጠምዘዝ ከሚሞክሩት አካላት አቅም በላይ መሆናችን በተጨባጭ አመላክቷል ብለዋል፡፡
የሃገራችን ሠላምና መረጋጋት የሚያሰጋቸው ኢትዮጵያን ለመበታተን የማይፈነቅሉት ድንጋይ እንደሌለ ርዕሰ መስተዳድሩ አስረድተዋል፡፡
ለሠላም ጽኑ አቋም ያለው የኢትዮጵያ መንግስት የሃገሪቱ ሠላም በአፍሪካ ህብረት አደራዳሪነት እንዲካሄድ ቁርጠኛ አቋም ይዞ እየተንቀሳቀሰ እንደሚገኝ ጠቅሰዋል፡፡
በየትኛውም መንገድ በሃገራችን ሉአላዊነት የሚገባ ማንኛውን አካል መንግስት አይታገስም ያሉት አቶ አሻድሊ፤ መላው የክልሉ ህዝቦች በሀገር ላይ የሚቃጣን ጥቃት ለመመከት ከመንግስት ጎን በመቆም የሚሰጡትን ድጋፍ አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጠይቀዋል፡፡
“ለኢትዮጵያ እቆማለሁ ድምጼን አሰማለሁ” ሰልፉ መሪ ሀሳብ ነው፡፡