አየር መንገዱ ያስገነባው ባለ አምስት ኮከብ ሆቴል በመጪው ታህሳስ አገለግሎት መስጠት ይጀምራል - ኢዜአ አማርኛ
አየር መንገዱ ያስገነባው ባለ አምስት ኮከብ ሆቴል በመጪው ታህሳስ አገለግሎት መስጠት ይጀምራል
የአዲስ አበባ መስከረም 14/2011 ኢትዮጵያ አየር መንገድ በ65 ሚሊዮን ዶላር ያስገነባውን ባለ አምስት ኮከብ ሆቴል በመጪው ታህሳስ ለአገልግሎት ክፍት እንደሚያደርግ አስታወቀ። የትራንስፖርት ሚኒስትር ሲራጅ ፈጌሳ ሆቴሉን ጨምሮ አየር መንገዱ እያስገነባ ያለውን የተርሚናል ማስፋፊያ ፕሮጀክት ጎብኝተዋል። የአየር መንገዱ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ተወልደ ገብረማሪያም በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት 'ስካይ ላይት' የተሰኘው ሆቴል 373 ክፍሎች አሉት። ሆቴሉ ዓለም አቀፍ ደረጃን የጠበቀ አገልግሎት ለደንበኞች እንዲያቀርብ ታስቦ መገንባቱንና በአፍሪካ በትልቅነቱ የመጀመሪያ የሆነ የቻይና ሬስቶራንት በውስጡ ማካተቱን ገልጸዋል። ቻይና የዓለም ትልቋ የቱሪስት አመንጪ አገር እንደመሆኗ የሬስቶራንቱ መኖር በርካታ ቻይናዊያን ወደ ኢትዮጵያ እንዲመጡ በር ይከፍታል ብለዋል። ኢትዮጵያን እንደ መሸጋገሪያ ተጠቅመው ወደ ሌሎች አገራት ለሚጓዙ መንገደኞች የተሟላ አገልግሎት በማቅረብ አገሪቱ ከዘርፉ ተጠቃሚ እንድትሆን እንደሚያደርጋትም አቶ ተወልደ አክለዋል። ሚኒስትር ሲራጅ ፈጌሳ በበኩላቸው "ሆቴሉ በቦሌ አለማቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ አቅራቢያ መገንባቱ የአየር መንገዱ ደንበኞች ሳይንገላቱ አገልግሎት እንዲያገኙ ያስችላል" ብለዋል። በሆቴሉ ውስጥ የኢትዮጵያ ባህላዊ ሬስቶራንት መኖሩ ደግሞ ኢትዮጵያን ዞረው የማየት እድል የሌላቸው ቱሪስቶች የአገሪቱን ባህላዊ እሴቶች በቀላሉ እንዲያውቁ እንደሚያግዝም አውስተዋል። የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአሁኑ ወቅት በአፍሪካ ቀዳሚ ደረጃን የያዘ ሲሆን 116 ዓለም አቀፍ መዳረሻዎችም አሉት።