ሠራዊቱ የኢትዮጵያን ሉዓላዊ እና የግዛት አንድነት በአኩሪ ጀግንነት በማስጠበቅ የህዝብ አለኝታነቱን አስመስክሯል- መጋቢ አብርሃም ኃይማኖት - ኢዜአ አማርኛ
ሠራዊቱ የኢትዮጵያን ሉዓላዊ እና የግዛት አንድነት በአኩሪ ጀግንነት በማስጠበቅ የህዝብ አለኝታነቱን አስመስክሯል- መጋቢ አብርሃም ኃይማኖት
ጥቅምት 12 ቀን 2015 (ኢዜአ) የሀገር መከላከያ ሠራዊት በከበረ መስዋዕትነቱ የኢትዮጵያን ሉዓላዊ የግዛት አንድነት በማስጠበቅና የህዝብ አለኝታነቱን በማስመስከር መቀጠሉን የኢሃፓ ተቀዳሚ ፕሬዚደንት መጋቢ አብርሃም ኃይማኖት ገለጹ።
የኢሃፓ ተቀዳሚ ፕሬዚደንትና በመስቀል አደባባይ የተካሄደው ህዝባዊ ሰልፍ አስተባባሪ መጋቢ አብርሃም ኃይማኖት ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በኢትዮጵያ ላይ እየተቃጣ ያለውን ጫና ለመመከት ኢትዮጵያውያን አደባባይ ወጥተው ድምጻቸውን አሰምተዋል።
በትዕይንተ ህዝቡ ላይም በኢትዮጵያ የሚቃጣን ማንኛውም አይነት ጫና መመከት እንደሚቻል ተግባራዊ መልዕክት እንደተላለፈ ገልጸዋል።
የፖለቲካ ድርጅቶች ምንም እንኳን የሃሳብ ልዩነት ቢኖራቸውም በኢትዮጵያ ሉዓላዊ አንድነት ላይ ሊቃጣ የሚችልን ማንኛውም አይነት ጫና ለመመከት ግን በአንድነት እንደሚነሱ ማሳየታቸውን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ጠላቶች የኢኮኖሚና የጦር ግንባር ጫና ፈጥረው የህዝቡን ጫና በማብዛት በእጅ አዙር ቅኝ ግዛት ለማስገባት ጥረት ቢያደርጉም አይሳካላቸውም ብለዋል።
በመላ ኢትዮጵያ የተካሄደው ትዕይንተ ህዝብም ለወዳጅ አገራት ተስፋን፤ ለጠላቶች ደግሞ የጥሞና ጊዜ እንዲወስዱ ማድረግ የቻለ መልዕክት መተላለፉን ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ ላይ ሦስተኛ ዙር ጦርነት የከፈተውን የአሸባሪው ህወሃትና የሸኔ ኃይል የጥፋት ተልዕኮ በማምከን በተባበረ ክንድ ሉዓላዊ አንድነቷ የተረጋገጠች ኢትዮጵያን እናስቀጥላለን ነው ያሉት።
የውጭ ባዕዳን ኃይሎች በጀግናው የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ላይ የሚያሰሙት መሰረተ ቢስ ጩኸትም የሰራዊቱን አኩሪ ተግባር ያላገናዘበና የሞራል ልዕልና እንደሌላቸው ማሳያ መሆኑን ተናግረዋል።
ሰራዊቱም በክቡር መስዋዕትነቱ የኢትዮጵያን ሉዓላዊ አንድነት እያስከበረ ያለ መመኪያ የህዝብ ልጅ ነው ብለዋል።
የፖለቲካ ድርጅቶችም ግንባር ላይ ከጠላት ጋር እየተፋለመ ለሚገኘው የህዝብ ልጅ ደጀን ለመሆን ከ32 ሚሊየን ብር በላይ የሚሆን የደጀንነት ድጋፍ ማድረጋቸውን አስታውሰዋልል።
የኢትዮጵውያ ዘብ ለሆነው የአገር መከላከያ ሰራዊት ድጋፋቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉም አንስተዋል።
ዛሬ በመላው ኢትዮጵያ “ለኢትዮጵያ እቆማለሁ፣ ድምጼን አሰማለሁ'' በሚል መሪ ሃሳብ አሸባሪውን ህወሃት የሚቃወም እና የአንዳንድ ምዕራባውያን ሀገራትን ጣልቃ ገብነት የሚያወግዝ ህዝባዊ ሰልፍ ተካሂዷል።