ቀጥታ፡

አዲሱ የኢነርጂ ፖሊሲ የግሉ ዘርፍ በስፋት ወደ ኢነርጂ ኢንቨስትመንት እንዲሰማራ የሚያስችል መሆኑ ተገለጸ

ጥቅምት 12 ቀን 2015 (ኢዜአ) አዲሱ የኢነርጂ ፖሊሲ የግሉ ዘርፍ በስፋት ወደ ኢነርጂ ኢንቨስትመንት እንዲሰማራ የሚያስችል መሆኑን በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የኢነርጂ ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ሱልጣን ወሊ ገለጹ።

በደቡብ አፍሪካ ኬፕታውን ከተማ የአፍሪካ ኢነርጂ ሳምንት በአፍሪካ የኢነርጂ ዘርፍ ኢንቨስትመንት አማራጮች ላይ ትኩረት አድርጎ ተካሂዷል።

በመድረኩ ላይ የኢትዮጵያ የኢነርጂ ፎረም ላይ ገለጻ ያደረጉት ሚኒስትር ዴኤታው በኢትዮጵያ ከምንግዜውም በላይ በኢነርጂ ኢንቨስትመንት መስክ ምቹ ሁኔታ መፈጠሩን አውስተዋል።

በተለይ ሀገራዊ ሪፎርሙን ተከትሎ ከግማሽ ምዕተ ዓመት በላይ ስራ ላይ የነበረው የኢነርጂ ፖሊሲ መከለስና ወደ ትግበራ ለመግባት በሂደት ላይ መሆኑን ገልጸው ፤ በተለይ የግል ዘርፉ ወደ ኢነርጂ ኢንቨስትመንት እንዲሰማራ የሚጋብዝ ነው ብለዋል፡፡

በሌላ በኩል በሂደት ላይ ሚገኘው የፓወር ሴክተር ሪፎርም መመሪያ በሚተገበርበት ወቅት ለኢነርጂ ኢንቨስትመንት ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥር ተናግረዋል።

የኢንቨስትመንት አዋጅ መሻሻል፤ ለሀገር ውስጥና ከሀገር ውጭ ለሚመጡ ባለሀብቶች፤ በኢነርጂ ኢንቨስትመንት ዘርፍ ለመሰማራት ምቹ ሁኔታ መፍጠሩንም አብራርተዋል፡፡

ሚኒስትሩ በማብራሪያቸው ኢትዮጵያ የምስራቅ አፍሪካ የሀይል ትስስር አባል ሀገር መሆኗ እና ሀይልን ለመሸጥ ምቹ ስትራጂካዊ አካባቢ ላይ እንደምትገኝ አንስተዋል።

በተካሄደው የአፍሪካ የኢነርጂ ሳምንት ውይይት ላይ በርካታ የሀገር መሪዎች፣ ባለሃብቶች፣ የዘርፉ ሚኒስትሮችና ሌሎች ባለ ድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም