በኢትዮጵያ ሉዓላዊነት ላይ የመጣን ማንኛውም ኃይል አንታገስም- የሱሉልታ ነዋሪዎች - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮጵያ ሉዓላዊነት ላይ የመጣን ማንኛውም ኃይል አንታገስም- የሱሉልታ ነዋሪዎች
ጥቅምት 12/2015(ኢዜአ) በኢትዮጵያ ሉዓላዊነት ላይ የመጣን ማንኛውም ኃይል አንታገስም ሲሉ በሱሉልታ በተካሄደው ህዝባዊ ሰልፍ ላይ የተገኙ የከተማዋ ነዋሪዎች ተናገሩ።
በሱሉልታ ከተማ የውጭ ሀይሎችን ጣልቃ ገብነትና አሸባሪው ህወሓት ኢትዮጵያን ለማፍረስ የሚያደርገውን እንቅስቃሴ የሚያወግዝ ሰልፍ ተካሂዷል።
በሰልፉ ላይ የከተማዋና የአካባቢው ነዋሪዎች የተሳተፉ ሲሆን በኢትዮጵያ ሉዓላዊነት ላይ የሚደረግን ጣልቃ ገብነት የሚያወግዙ መልዕክቶችም ተላልፈዋል።
ኢትዮጵያ ችግሮቿን ለመፍታት የውጭ ጣልቃ ገብነት አያሻትም፤ መንግስት ሰላምና አንድነትን ለማስጠበቅ የሚወስደውን እርምጃ እንደግፋለን፤ አሸባሪው ህወሃት የትግራይና የኢትዮጵያ ህዝብ ፀር ነው የሚሉ መልዕክቶች ተላልፈዋል።
ለኢዜአ አስተያታቸውን የሰጡ የሰልፉ ተሳታፊዎች፤ የኢትዮጵያ ችግር የሚፈታው በኢትዮጵያዊያን ብቻ ነው፣ በሉዓላዊት አገር ውስጥ ጉዳይ ጣልቃ የሚገባን አካል በጋራ በመሆን ማስቆም ይገባናል ሲሉ ገልጸዋል።
ከአስተያየት ሰጪዎቹ መካከል ወይዘሮ ትዕግስት ዓለሙ "አሸባሪው ህወሓት ወረራ በፈጸመባቸው በአማራና አፋር ክልሎች ዜጎችን ለስቃይ ሲዳርግ ቃል ያላወጣ አካል ዛሬ ሉዓላዊነታችንን ለማስከበር ስንነሳ አለሁ ማለቱ ትዝብት ውስጥ ይከታል" ብለዋል።
ኢትዮጵያን ለማፍረስ እየሰሩ ያሉ አካለትን በመመከትና አንድነታችንን በማጠናከር እንደሁልጊዜው ሉዓላዊነታችንን ማስከበራችን ይቀጥላል ሲሉ ተናግረዋል።
ወጣት ቶኩማ ቢልሳ በበኩሉ የኢትዮጵያዊያን ችግር የሚፈታው በኢትዮጵያዊያን ብቻ ነው፤ ኢትዮጵያ በታሪክ ለውጭ ጠላት ተንበርክካ አታውቅም የአባቶቻችንን ታሪክ እንደግመዋለን ብሏል።
ሌላው አስተያየት ሰጪ አቶ አንበሴ ይማም የኢትዮጵያ ጸጥታ ሃይል ከህዝቡ ጋር በመሆን ለሚከፍለው መስዋዕትነት ትልቅ ክብርና ቦታ እንዳላቸው ገልጸዋል።
ሌላዋ የሰልፉ ተሳታፊ ወይዘሮ ዳዊቲ ደቀባ በበኩላቸው ኢትዮጵያን ለማፍረስ እየሰሩ ያሉ አካላት ከኢትዮጵያ ላይ እጃቸውን ሊያነሱ እንደሚገባ ተናግረዋል።