ቀጥታ፡

በህዝቦቿ አንድነት የተመሰረተች ኢትዮጵያ በህብረ ብሄራዊነቷ ጸንታ ትቀጥላለች

አለታ ወንዶ፣  ጥቅምት 12/2015 (ኢዜአ) በህዝቦቿ አንድነት የተመሰረተች ኢትዮጵያ በህብረ ብሄራዊነቷ ጸንታ ትቀጥላለች ሲሉ በብልፅግና ፓርቲ የሲዳማ ክልል ጽህፈት ቤት የአደረጃጀት ዘርፍ ሀላፊ አቶ አሸናፊ ኤሊያስ አስታወቁ።

የውጭ ጣልቃ ገብነትንና የአሸባሪውን እኩይ ተግባር የሚያወግዝ የተቃውሞ ሰልፍ በሲዳማ ክልል በአለታ ወንዶ ተካሂዷል።

በሰልፉ ማጠቃለያ ንግግር ያደረጉት በብልፅግና ፓርቲ የሲዳማ ክልል ጽህፈት ቤት የአደረጃጀት ዘርፍ ሀላፊ አቶ አሸናፊ ኤሊያስ አሸባሪው የህወሀት ቡድን በተደጋጋሚ በሀገሪቱ ላይ የከፈተው ጦርነት እኔ ያልመራኋት ኢትዮጵያ ትፍረስ ከሚል እሳቤ መነሻ ነው።

"በህዝቦቿ አንድነት የተመሰረተች ኢትዮጵያ ህብረ ብሄራዊነቷን ጠብቃ በጽናት ትቀጥላለች" ያሉት ሀላፊው ኢትዮጵያዊነት ለመላው አፍሪካዊያን ምሳሌ የሚሆን አንድነት እንደሆነም ገልጸዋል።

"ያለንን እምቅ ሀብት ተጠቅመንን የብልጽግና ጉዟችንን እንዳናረጋግጥ የሚጥሩ ጠላቶቻችንን በጋራ መመከት ይገባናል" ብለዋል።

"በገፉን ቁጥር አንድነታችን እየጠነከረ ብልፅግናችንን እያረጋገጥን ለህዝቦቿ ምቹ ሀገር እንፈጥራለን" ሲሉም አክለዋል።

የክልሉ ሴቶች፣ ህፃናትና ወጣቶች ቢሮ ሀላፊ ወይዘሮ እመቤት ኢሳያስ በበኩላቸው የኢትዮጵያ ሴቶች በታሪክ  ሀገር ስትደፈር ንቁ ተሳታፊ መሆናቸውን አስታውሰዋል።

ሀገር ተገዳ በገባችው ጦርነትም የሲዳማ ሴቶች ለመከላከያ ሰራዊት የተለያዩ ድጋፎች ማድረጋቸውን ገልጸው "አሁንም በሀገር የተቃጣውን እኩይ ተግባር በመቃወም ትግላችንን እንቀጥላለን" ብለዋል።

"የተከፈተብንን ጦርነት ከመመከት ጎን ለጎን የተጀመሩ ልማቶችን በማጠናከር ተጠቃሚነታችንን እናረጋግጣለን፤ ብልጽግናችንን እናስቀጥላለን" ብለዋል።

አሸባሪው ህወሓት ዳግም ለሶስተኛ ጊዜ የከፈተውን ጦርነት በመመከት ህግ በማስከበር ዘመቻ ለተሰማራው የሀገር መከላከያ ሰራዊት ደጀንነታችንን በማጠናከር በሁለንተናዊ መልኩ ስኬታችንን እናስቀጥላለን ስሉ ገልጸዋል።

የአለታ ወንዶ ከተማ ከንቲባ አቶ ጌዳሁን ጋቢሶ በበኩላቸው በሀገር የተቃጣውን እኩይ ተግባርና የውጭ ጣልቃ ገብነት ለመቃወም በሰላማዊ ሰልፍ ድምጹን ላሰማው ህዝብ ምስጋና አቅርበዋል።

"አሸባሪው ለሶስተኛ ጊዜ በከፈተው ጦርነት የሚከፈለውን መስዋእትነት በመክፈል ጭምር አንድነታችንን እናጠናክራለን" ብለዋል።

የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎችና የህብረተሰብ ተወካዮችም መልእክት አስተላልፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም